
የሕዝብ ቁልፍ መሰረተ ልማት (Public Key Infrastructure) ለመረጃ ታማኝነትና ሀገራዊ ሉዓላዊነት መሠረት!
የዘመናዊው ዓለም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ያለ “ዲጂታል እምነት – Digital Trust” ሊታሰብ አይችልም። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በራስ አቅም የገነባው የሕዝብ ቁልፍ መሰረተ ልማት (Public Key Infrastructure – PKI) የዚህ እምነት የማዕዘን ድንጋይ ነው።
የኢትዮጵያ የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ግብን ለማሳካት PKI የሚከተሉትን ሚናዎች ይጫወታል፡-
• ዲጂታል ማንነት (Digital ID): ዜጎች በማንኛውም የኦንላይን አገልግሎት ላይ ማንነታቸውን በታማኝነት እንዲያረጋግጡ ያስችላል።
• ዲጂታል ፊርማ (Digital Signature): በአካል ተገኝቶ የመፈረምን አስፈላጊነት በማስቀረት፣ በዲጂታል መንገድ የሚፈረሙ ሰነዶች የህግ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያደርጋል።
• ኢ-መንግስት (e-Government): የመንግስት ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን በኢንተርኔት ሲሰጡ የመረጃ ስርቆት እንዳይኖር እና ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ ግንኙነት እንዲኖር ያደርጋል።
እንደ ኢስቶኒያ እና ሲንጋፖር ያሉ በዲጂታላይዜሽን ቀዳሚ የሆኑ ሀገራት ስኬታቸው ሚስጥር ጠንካራ የPKI ስርዓት መዘርጋታቸው ነው። በእነዚህ ሀገራት ዜጎች ከቀረጥ ክፍያ እስከ ምርጫ ድምጽ መስጠት ድረስ ያሉ ስራዎችን ከቤታቸው ሆነው በPKI ደህንነቱ በተጠበቀ የዲጂታል ፊርማ ያከናውናሉ። ይህ አሰራር ቢሮክራሲን ይቀንሳል፣ ሙስናን ይከላከላል፣ እንዲሁም ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ ታማኝ የዲጂታል ስነ-ምህዳር ይፈጥራል።
PKI መሠረተ ልማት ለአንድ ሀገር የደህንነት ዋስትና ነው፤ ምክንያቱም፡-
1. የመረጃ ታማኝነት (Integrity): መረጃ ከላኪው ወደ ተቀባዩ እስኪደርስ ድረስ ሳይበረዝ እና ሳይቀየር መድረሱን ያረጋግጣል።
2. አለመካድ (non-repudiation): አንድ ግለሰብ በዲጂታል መንገድ የፈጸመውን ተግባር “እኔ አልፈጸምኩም” ብሎ እንዳይክድ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ማረጋገጫ ይሰጣል።
3. የመረጃ በላይነት (Information Superiority): የሀገራችንን ወሳኝ መረጃዎች በራሳችን ቁልፍ እና ምስጠራ (Encryption) መጠበቃችን የውጭ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ዲጂታል ሉዓላዊነታችንን ለማስከበር ያስችላል።
በአጠቃላይ PKI ተቋማት ውጤታማነታቸውን እንዲያሳድጉ፣ የፋይናንስ ስርዓታችን በቴክኖሎጂ እንዲዘምን እና ኢትዮጵያ በዲጂታል ጉዞዋ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችል የቴክኖሎጂ ስኬት ነው።
የPKI አገልግሎት በተለይም ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹ መረጃዎችን ለሚይዙ እና የደንበኞችን እምነት ለሚፈልጉ ተቋማት ወሳኝ ነው። የፋይናንስ ተቋማት (ባንኮች እና ኢንሹራንሶች) ደህንነቱ የተጠበቀ ግብይት ለመፈጸም፣ የጤና ተቋማት የሕሙማንን ሚስጥራዊ መረጃ ለመጠበቅ፣ የፍትህ አካላት የህግ ሰነዶችን በዲጂታል መንገድ ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም የቴሌኮም እና የትምህርት ዘርፎች አገልግሎቶቻቸውን ወደ ዲጂታል ለመቀየር ይህንን መሰረተ ልማት መጠቀም ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም የታክስ እና የጉምሩክ ስርዓቶችን ይበልጥ ቀልጣፋ እና ከማጭበርበር የጸዱ ለማድረግ PKI ዋነኛ መፍትሄ ነው።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር












