
ዘንድሮ “ሹዋሊድ ለሕብረ ብሔራዊ አንድነታችን እና ለቱሪዝም እድገታችን” በሚል መሪ ሀሳብ በዓሉ በድምቀት እንደሚከበር የሀረሪ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መግለጫ ያመለክታል።
የሹዋሊድ ክብረ በዓል ሰላምን፣ አብሮነትንና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ይከበራልም ነው የተባለው።
ቢሮው መግለጫው፣ በዓሉ በሀረሪ ብሔረሰብ ዘንድ ለምዕተ ዓመታት ሲከበር የኖረ፤ በትውልድ ቅብብሎሽ ባህሉንና ወጉን ጠብቆ ከነክብሩ ዛሬ ላይ የደረሰ እንደሆነ አመልክቷል።
በዓሉ ሰላምን፣ አብሮነትን እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ያለው የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ፣ ከበዓሉ በተጨማሪ በሀረር ከተማ የባህል፣ ፌስቲቫል እና አውደ ርዕይ፣ የልማት ስራዎች ጉብኝትን ጨምሮ ሌሎች መርሐ ግብሮች ይከናወናሉ።
የሹዋሊድ በዓል አከባበር ከሕዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል።
የአብሮነት ዕሴትን እያጎለበቱ ከሚገኙ ባህላዊ በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን በተለይም በምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል የባህል ትውውቅ በመፍጠር የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በዓሉ የቱሪዝም ዘርፍ እንዲጎለብት ከማድረግ አንፃርም የላቀ ጠቀሜታ አለው።












