NBC Ethiopia
February 10, 2026
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀሙን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል። በ2025/26 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀሙን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በግማሽ ዓመት ብቻ 4 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ማትረፉን አስታውቋል።

ይህም የእቅዱን 2 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ነው የተገለፀው፡፡ የአየር መንገዱን የስራ አፈፃፀም አስመልክቶ ሪፖርት ያቀረቡት የአየር መንገዱ ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በስድስት ወራት ውስጥ 3 አዳዲስ መዳረሻዎችን በመጨመር ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ወደ 145 ከፍ ማለታቸውን አስታውቀዋል።

የያቤሎ የአየር መንገድን መመረቁን ተከትሎ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎቹን ወደ 23 ማሳደጉን አስታውቀዋል።
በስድስት ወራት ውስጥ ከ10 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን መጓጓዝ መቻሉን የተነገረ ሲሆን፤ የእቅዱን 11 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል። 451 ሺ ቶን የጭነት አገልግሎት መስጠቱን ሲገለፅ ከእቅዱ 4 በመቶ ብልጫ አለውም ተብሏል።

የመሰረተ ልማት ማስፉፊያ ስራዎች ከቦሌ አየር ማረፊያ አንስቶ በተለያዩ ከተሞች ባሉ ኤርፖርቶች እየተሰሩ ነው ተብሏል። በዚሁ ዓመት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በቢሾፍቱ የመሰረተ ድንጋይ መጣሉ አየር መንገዱ ካስመዘገባቸው ዐበይት ስኬቶች መካከል ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ አዲስ ዋና መስሪያ ቤት ማስገንባት መጀመራቸውንም ተናግረዋል።

አየር መንገዱ መሰል ስኬቶችን ያስመዘገበው በበርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፈ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገልፀዋል። የአውሮፕላን እጥረት፣ የአየር ሁኔታና፣ የአሜሪካ መንግስት አዲስ የቪዛ ፓሊሲዎችና እገዳዎች አየር መንገዱ ፈታኝ ከሆነበት ተግዳሮቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በ-የአብስራ ሚሊዮን












