
ከተመሰረት 15 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ያከናወናቸው ስራዎችን እንዲሁም በቀጣይ የሚሰራቸው ተግባራትን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማብራሪያ ሰጥቷል።
ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) የግብርናው ዘርፍ ለማዘመንና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያመላክቱ ጥናቶችን ሲያከናውን መቆየታቸውን አንስተዋል።
በዚህም ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለመሸጋገር የሚያግዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው አመልክተዋል።
በቀጣይም ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ወደ ገጠር ትራንስፎርሜሽን የተሻገረ ገጠር ለመፍጠር ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል። ይህም አርሶ አደሩ ትርፍ ምርት እንዲያመርት፤ የገጠር መሰረተ ልማት ለማጠናከር ብሎም የገጠር ማህበረሰቡን ገቢ ለማሻሻል እንደሚያግዝ ነው የገለጹት።
እንዲሁም ግብርናው በቴክኖሎጂ በማገዝ ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ባለፉት 15 ዓመታት ተቋሙ ካካሄዳቸው ጥናቶች 80 በመቶ የሚሆኑት ወደ ተግባር መግባታቸው ተመላክቷል።
ኢንስቲትዩት በሚሰራቸው ስራዎች ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 6 በመቶ አበርክቶ እንዳለው ተጠቁሟል።
በሰላም ይልማ












