
የሙያ ምዘናና ሰርተፍኬሽን ሂደትን ሙሉ በሙሉ አውቶሜት (Automated) በማድረግ ላይ አተኩሮ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል::
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሙያ ደረጃና ሥርዓተ ስልጠና ዝግጅት እና ብቃት ምዘና መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ማርታ ወልዴ እንደገለጹት፣ አሠራሩ አውቶሜት መደረጉ ከብቃት ምዘናና ሰርተፍኬት አሰጣጥ ረገድ በዘርፉ ለዓመታት ሲስተዋሉ የነበሩ በርካታ ችግሮችን በዘላቂነት ይፈታል።
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ ሥራው በድጅታል አሠራር መመራቱ በእጅ የሚሰሩ አሰራሮችን በማስቀረት የሐሰተኛ ሰርተፍኬቶችን ስርጭት መከላከል ያስችላል ብለዋል።
አክለውም የምዘና፣ ምዝገባ፣ የውጤት መግለጫና የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት አሰጣጥ ሂደትን ከማፋጠን ባሻገር የምዘና ሂደቱንና የሰልጣኞችን መረጃ በአንድ ማዕከል በማደራጀት ለሥራ ገበያው ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ እንደሚያስችልም ገልፀዋል::
ሚኒስቴሩ የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን የዜጎችን እንግልት ለመቀነስና ግልጽነት የሰፈነበት አሰራር ለመዘርጋት የጀመረውን የሪፎርም ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል::












