
ባለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ የሳውዲ አረቢያ ግዛቶች በበረዶ ተሸፍነዋል።
ይህ በሀገሪቱ የተከሰተው ብርቱ የአየር ሁኔታ፣ በበረሃ የተከበቡትን የሳውዲ ተራራዎች ወደ አስደናቂ የክረምት መልክዓ-ምድር ቀይሯቸዋል።
የዚህ ያልተለመደ አየር ጸባይ ምክንያት የሆነው ኃይለኛ የቀዝቃዛ አየር ሞገድ፤ ብርቱ ነፋስና ዝናብ ይዞ የመጣ ሲሆን፣ በሰሜናዊው የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ደግሞ የበረዶ ዝናብ እንዲከሰት አድርጓል።
በሃገሪቱ ተራራማ ቦታዎች፣ የሙቀት መጠኑ ከዜሮ በታች 4 ዲግሪ ሴልሺየስ ድረስ ዝቅ ያለ ሲሆን ይህም ከባህር ጠለል በላይ በ2,600 ሜትር ከፍታ ላይ በረዶ እንዲከማች አስችሏል።
የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ክስተቱን “ታሪካዊ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ በማህበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ምስሎች እና ቪዲዮዎችም የተራራ ሰንሰለቶች በነጭ በረዶ ተሸፍነው አሳይተዋል።

በረዶ በጣለባቸው አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች በዚህ ብርቅዬ የአየር ሁኔታ ለመደሰት ወደ ውጭ በመውጣት በበረዶው ላይ ስኪንግ (skiing) ሲያደርጉ እና ፎቶ ሲነሱ ታይተዋል።
ይህ የቀዝቃዛ አየር ሞገድ ከበረዶው በተጨማሪ በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች ከባድ ዝናብ እንዲጥል ያደረገ ሲሆን፣ ይህም ክስተቱን ይበልጥ ልዩ አድርጎታል።












