NBC Ethiopia
December 2, 2025
ከጥቂት ስራዎች ኋላ በምስራቅ አፍሪካ ግዙፉን የካፒታል ገበያ መፍጠር የሚያስችል ጉዞ ላይ ነን አሉ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር

ሁለተኛው አለም አቀፍ የካፒታል ገበያ ጉባኤ በአዲስ አለም አቀፍ ኮንቬንሽን እየተካሄደ ነው። ጉባኤው “ከመሰረት እስከ ከፍታ፤ ለወደፊት አካታች የፉይናንስ ስርአት ሰዎችና ገበያን ማብቃት” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው። በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተክሉ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝና፣ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ተገኝተዋል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣናት ዋና ዳይሬክተር ሀና ተክሉ የካፒታል ገበያው በአዋጅ ቁጥር 1248/2013 ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ጠንካራና አካታች፣ ሁሉን አቀፍ የካፒታል ገበያ ስርአትን እንዲኖር እየሰራ ነው ብለዋል። ተቋሙ ሌሎች ሀገራት ስርአቱን ለመገንባት የፈጀባቸውን ረዥም አመታት ባጭር ጊዜ የተቀናጀ ስራ በመስራት ስኬት ማስመዝገቡንም ገልፀዋል።

ባለፉት አመታት በተከናወኑ ስራዎች የካፒታል ህግ ስርአት መሰረት መጣል፣ ላይሰንስ የመስጠትና፣ የፉይናንስ ግንዛቤ በየዘርፉ የመስጠት ስራን ጨምሮ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። የብሄራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው የካፒታል ገበያ ስርአት ለእያንዳንዱ ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ ነው ያሉ ሲሆን በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እድገትን ካስመዘገቡ ዘርፎች ቀዳሚው ነው ብለዋል።
የካፒታል ገበያ ስርአት ለእያንዳንዱ የኢኮኖሚ ዘርፍ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል ያሉ ሲሆን የካፒታል ገበያ መመስረቱ በባንክ ላይ ተንጠልጥሎ የነበረውን የገበያ ስርአት በእጅጉ መቀየር ችሏል ብለዋል። የካፒታል ገበያ ምስረታ በድንገት የመጣ ሳይሆን በርካታ ጠንካራ ጥናትና ስራዎችን በማከናወን የተገኘ ተቋም ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሁለተኛው አለም አቀፍ የካፒታል ጉባኤ ባለፉት አመታት የተሰሩ ስራዎች የሚቀርቡበት፣ ከአለም አቀፍና አህጉራዊ የካፒታል ገበያ ተቋማት ጋር ልምድ የሚለዋወጡበት ፣ ባለፉት አመታት በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እድገት ለተሳተፉ አካላት እውቅና የሚሰጥበት ይሆናል። ጉባኤው ለሶስት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።












