የዓለማችን ረጅሙ ስም ያለው አውስትራሊያዊ ከ2,000 በላይ ቃላትን የያዘውን ሙሉ ስሙን በማንበብ አስደምጧል። ይህን ለማጠናቀቅም ከአንድ ሰዓት በላይ እንደፈጀበት ይናገራል።
እ.ኤ.አ በመጋቢት 1990 ዓ.ም ስሙ ውስጥ 2,251 የመሃል ስሞች እንዲኖሩት አድርጎ ያስቀየረው ላውረንስ ዋትኪንስ፣ በድምሩ 2,253 የተለያዩ ቃላት የያዘ የዓለማችን ረጅሙን ስም በማስመዝገብ በጊነስ ወርልድ ሪከርድስ የዓለም ክብረ ወሰንን አግኝቷል።
ዋትኪንስ እንዳለው በሠርጉ ላይ የሥነ ሥርዓቱ አስፈጻሚ ሙሉ ስሙን ለማንበብ 20 ደቂቃ ያህል ወስዶበታል። ሆኖም ራሱ ለጊነስ ወርልድ ሪከርድስ በላከው ቪዲዮ የራሱን ስም ለማንበብ ከአንድ ሰዓት በላይ ፈጅቶበት ነበር።
ስሙ የሚጀምረው እንዲህ በሚሉ ስሞች ነው፡- Laurence Alon Aloys Aloysius Alphege Alun Alured Alwyn Alysander Ambie Ambrose Ambrosius Amias Amiot Amyas Anders Andre Andrea Andreas Andrew Andy Aneirin Anguish Anleifr – እነዚህም በ”A” ፊደል ከሚጀምሩት ስሞች ውስጥ የተወሰኑት ብቻ ናቸው።
ለጊነስ ወርልድ ሪከርድስ በሰጠው ቃል “አንዳንድ ሰዎች የሚያስመዘግቧቸው ለየት ያሉና ያልተለመዱ ሪከርዶች ሁልጊዜ ይማርኩኝ ነበር። እኔም የዚያ አካል መሆን በጣም እፈልግ ነበር” ብሏል።
አክሎም፣ “የጊነስ ወርልድ ሪከርድስ መጽሐፍን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻ አንብቤ ላሸንፍበት የምችለውን ሪከርድ መኖሩን ለማየት ሞከርኩ፤ ያገኘሁት ብቸኛው ሪከርድ ደግሞ ከአሁኑ የሪከርድ ባለቤት የበለጠ ስም መጨመር ነበር” ሲል ገልጿል።
የስም ለውጡ ሂደት ብዙ የሰነድ ሥራ እና ወደ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ መመላለስ እንደጠየቀው ተናግሯል። ስሙን በተሳካ ሁኔታ ከቀየረ በኋላ፣ ሌሎች የእሱን ሪከርድ እንዳይሞክሩ የሚከለክሉ አዳዲስ ሕጎችም ወጥተዋል።
ላውረንስ እንደሚለው “ከስሞቼ ውስጥ የምወደው ደግሞ AZ2000 የሚለው ነው። ምክንያቱም ከ’A’ እስከ ‘Z’ ያሉ ፊደላትን የያዙ 2,000 ስሞች አሉኝ ማለት ነው።” ብሏል።
ዘገባው የዩፒአይ ነው።
በ – ዳንኤል መኮንን












