ኢንዱስትሪው በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ ምርቶችን በማምረት የመንግስትን የግዥ ፍላጎት ማሟላት የሚችልበት ዕድል መፈጠሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ።
በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የተዘረጋው ዘመናዊ የግዥ ሥርዓት ለአምራች ዘርፉ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በተመለከተ ለዘርፉ ተዋንያን ገለጻ እየተደረገ ነው። በመድረኩ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው አስቻይ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው ዘርፎች አንዱ አምራች ኢንዱስትሪው መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት የኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሕግና አሰራር ማሻሻያዎችን ከማድረግ ባለፈ የገበያ ትስስርን ለማሳደግ ተጨባጭ ሥራዎች እየሰራ ይገኛል ብለዋል። ከዚህ አኳያ፣ አሁን ያለው የመንግስት ግዥ መመሪያ የሀገር ውስጥ አምራችነትን የሚያበረታታና የገቢ ምርትን ለመተካት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑን አንስተዋል።
መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ የሀገር ውስጥ ግዥን በስፋት እየተጠቀመ ቢሆንም የግዥ መመሪያውንና አሰራሩን በአግባቡ አለመጠቀም እንደሚስተዋል አመልክተዋል። የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሰረት መስቀሌ በግዥ ሥርዓቱ ለአምራች ኢንዱስትሪው የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
በተለይም የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱ ቀልጣፋና ፈጣን መሆኑን ጠቅሰው፤ የመንግስት ተቋማት ጥራት ያላቸው ምርቶችን ከሀገር ውስጥ አቅራቢዎች እንዲያገኙ እያደረገ ነው ብለዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።












