ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የቻይናው ሺ ጂንፒንግ በሚቀጥለው ሳምንት ሊገናኙ መሆኑን ዋይትሀውስ ዕወቁልኝ አለ።
መሪዎቹ በፈረንጆቹ ጥቅምት 30 በደቡብ ኮሪያ የሚገናኙ ይሆናል። ፕሬዚዳንት ሺ እና ትራምፕ በ2019 በሪፐብሊካኑ የመጀመሪያ ዙር የስልጣን ዘመን ወቅት ነበር ለመጨረሻ ጊዜ በአካል የተገናኙት።
የዋይትሀውስ ፕረስ ሴክሬታሪ ካሮላይን ልቪት ትራምፕ በኤዥያ ጉዟቸው ሺን ያገኟቸዋል በሚል አረጋግጠዋል። ወደ ማሌዥያና ደቡብ ኮሪያ ብቅ የሚሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ የጉዟቸው ዋና ዓላማ በኤዥያ-ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ጉባዔ (APEC) ላይ መሳተፍም ነው ።
መሪዎቹ በምን በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገሩ ዝርዝር ይዘቶችን ካሮላይን ልቪት ባያጋሩም የንግድ እና የኢንዶ-ፓስፊክ ቀጠና ጉዳዮች ይነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ትጥቅ ጉዳይም የሚነሳ ይሆናል።
ዶናልድ ትራምፕ ከመቶ በመቶ በላይ በቤይጂንግ ምርቶች ላይ ታሪፍ እጥላለሁ ባሉበት ሰዓት ነው ለነገሮች መፍትሄ እንሰጣለን በጎን እያሉ የሚገኙት። በሌላ በኩል ዋይት ሀውስ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ቭላድሚር ፑቲን መካከል ሊደረግ የታሰበው ውይይት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል ማለት እንዳልሆነም አስገንዝቧል ።
ዘገባው የአር ቲ ነው
በ-ቢኒያም ካሴ












