የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ አፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በስዊድን እና እንግሊዝ በአካል በመገኘት አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ማጠናቀቁ ገልጿል።
ኮሚሽኑ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ከዲያስፖራው አጀንዳን የመሰብሰብ እና ተሳታፊ የመምረጥ ሂደት ውጤታማ እንደነበር ጠቁሟል።
ሆኖም በራሳቸው ምክንያቶች የተለየ ሀሳብ አለን የሚሉ ወገኖች በመድረኩ እንዲሳተፉ ጥረት ተደርጎ ሀሳባቸውን ቢገልጹም የተወሰኑ ዜጎች አዳራሽ ለመግባት ፍቃደኛ እንዳልነበሩ ነው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ የገለጹት።
የነበረው ሁኔታ ግን በምክክር ሂደት ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ አለመኖሩ ነው የተገለጸው። በውጭ የሚገኙት ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውን ስለ ኮሚሽኑ አካታችነት፣ አሳታፊና ግልጽ አካሄዱን የተመለከቱ ማብራሪያዎች እንደቀረበላቸውም ተነስቷል።
ከዲያስፖራው በአካል በመገኘት የሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ቢጠናቀቅም በበይነ መረብ ሀሳቦችን የመቀበል ሂደት እንደሚቀጥል ተጠቁሟል። ከኮሚሽኑ ቀሪ ስራዎች መካከል የትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ አንዱ ሲሆን በክልሉ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በ2 ዙር በተደረጉ ውይይቶች መሰረት ሂደቱን የተሳካ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል።
በሰላም ይልማ












