የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በኒውዮርክ 80ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ የኢትዮጵያን አቋም ባቀረቡበት ንግግራቸው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትን ለማሻሻል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ እና በማሻሻያው ለአፍሪካ ውክልና በምክር ቤቱ በሁለቱም በኩል ቅድሚያ እንዲሰጥ ድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
ክቡር ፕሬዝዳንቱ ለአፍሪካ የረጅም ጊዜ የፍትሕ መሻት ጥያቄ አቋራጭ ወይም ግማሽ መፍትሔ እንደሌለ ገልጸዋል።
ክቡር ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ትኩረት ከሰጧቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው ዕዳን የተመለከተ ሲሆን በዕዳ ሥረዛ ዙሪያ አዲስ ዓለም አቀፍ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል። በተለይ አፍሪካን ኢላማ ያደረጉ የኃይል እና የንግድ እቀባ እርምጃዎች በአፋጣኝ እንዲነሱ ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ በቀጣናችን ያለውን ዓለም አቀፍ ጸረ ሽብር ዘመቻ አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉ ሲሆን ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በተለይ በሶማሊያ ለተሰማራው የአፍሪካ ህብረት ድጋፍ ሰጭ እና አረጋጊ ኃይል ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ የናይልን ወንዝ በተመለከተው የንግራቸው የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ባለፈው ጥቅምት 2024 ወደ ተግባር መግባቱን አስታውሰው :የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽንም ወደ መቋቋም ደረጃ መቃረቡን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቁም ኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ላልሆኑ 60ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ንጹህ የኃይል ምንጭ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ብለዋል። ግድቡ በከባድ የውኃ እጥረት ውስጥ ለሚኖሩ ወገኖቻችን ንጹህ ውሃ ለማቅረብ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና አጠቃላይ ልማትን እውን ለማድረግ አቅማችንን ያሳድጋል ብለዋል።
ግድቡ ለሰፋፊ ክልላዊ ትስስር ተስፋን የሚፈጥር እንደሆነ እና በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኘው ከፍተኛ ድጋፍ እና ትብብር በናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ትብብር ለመፍጠር የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
የባሕር ጉዳይን በተመለከተ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛ ትልቅ የሕዝብ ብዛት ያላት እና ከፍተኛ የባሕር ንግድ ያላት በቀይ ባህር እና በህንድ ውቅያኖስ የባሕር ላይ የባሕር ጉዞ ደኀንነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥም ፕሬዝዳንት ታዬ ገልጸዋል።
በመልክዓምድራዊ ሁኔታዎች ምክንያት የትኛውም ሀገር የእድገት፣ የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ እድሎች ዝግ መሆን እንደሌለበት ዋና ፀሐፊው በአዋዛ ጉባኤ ላይ ከሰጡት መግለጫ ጋር ተስማምተናል።
ከፍተኛ ባሕርን የሰው ልጅ የጋራ ቅርስ አድርጎ የሚገልጸው እና ሁሉንም አገራት በእኩልነት የመጠቀም መብትን የሚያረጋግጥ የዓለም አቀፍ ሕግ ከፍተኛው እውነታ እውን መሆን አለበት።
ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር በመሆን በቀይ ባሕር እና በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ የሚገኙ ሁሉም አገሮች እኩል ልማት እና ደኀንነትን ማረጋገጥ ወደሚያስችል ሁለንተናዊ አሰራር እንዲዘረጋ እንደምትሰራ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ይህንን ሕጋዊ ፖሊሲዋን ለማሳካትም የዲፕሎማሲያዊ እና ሰላማዊ አማራጮችን እንደምትከተል ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ገልጸዋል። ክቡር ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ሌሎች ቀጣናዊ ፣አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በማካተት የኢትዮጵያን አቋም ገልጸዋል።












