የእስራኤል ጦር በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ ላይ የአየር ጥቃት አደረሰ።
አይ ዲ ኤፍ በሰንዓ የሁቲዎችን ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ መምታቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን ከየመን ለሚሰነዘርብኝ ተደጋጋሚ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ያደረኩት ነው ሲልም መግለጫ አውጥቷል። ከሁቲዎች ጋር አብሮ የሚሰራው አል-ማሲራህ ቴሌቭዝን ጥቃቱ መድረሱን እና አካባቢው ላይ ከባድ ፍንዳታ እንደነበርም ዘግቧል።
የተወሰደውን እርምጃ የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ያረጋገጡ ሲሆን በርካታ የጦር አውሮፕላኖች እና የአየር ላይ አጋዦች እንደተሳተፉበትም አሳውቀዋል። የሁቲ ጦር ማዘዣ ዋና መስሪያ ቤት ዒላማ መሆኑም ተወስቷል። የሁቲዎች የደህነነት እና የመረጃ ቁሶች መመታተቸውን ጭምር ነው አይ ዲ ኤፍ ይፋ ያደረገው።
የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒሰትር እስራኤል ካትዝ በርካታ የሁቲ ኃይሎችን ህይወት ቀጥፈናል ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ሲጽፉ ከሁቲ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሚዲያዎች ደግሞ ሁለት ሰዎች ህይወታቸውን አተዋል ፤48ቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል በሚል ዘግበዋል።
ጥቃቱ የደረሰው የሁቲው መሪ አብዱል ማሊክ አል ሁቲ በቴሌቭዝን ጋዜጣዊ መግለጫ እየሰጡ በነበረበት ሰዓት ነው። የወታደራዊ ክንፉ የፕሮፓጋንዳ ክፍል እና የጦር መሳሪያ የተካማቸበት ቦታ ዒላማ ውስጥ መግባቱ ተነግሯል።
ሁቲ በቀይ ባህር ዳርቻ ኢላት የወደብ ከተማ ላይ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት አድርሶ 22 ሰዎች መጎዳታቸውን ተከትሎ የተሰጠ አጸፋዊ ምላሽ ነውም ተብሏል።
ዘገባው የአልጀዚራ እና ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ነው
በ-ቢኒያም ካሴ












