የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የጋዛ ነዋሪዎች ከተማዋን“አሁን ለቃችሁ ውጡ” ሲሉ አስጠነቀቁ።
የእስራኤል ጦር ለመሬት ጥቃት ዝግጅት እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋዛ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን “አሁን ለቃችሁ ውጡ” የሚል ከባድ ማስጠንቀቂያ ነው የሰጡት።
ኔታንያሁ ይህ ያሉት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ እስራኤል የጅምላ ግድያ እየፈጸመች ነው እንዲሁም የሰብአዊ እርዳታን ሆን ብላ እያገደች ነው ሲሉ እስራኤልን ካወገዙ በኋላ ነው።
ቮልከር ቱርክ ሰኞ እለት ባወጡት መግለጫ እስራኤል “ከጦር ወንጀል በላይ የሆኑ ወንጀሎችን” እየፈጸመች ነው ሲሉ ከሰዋል። በጋዛ ያለው ውድመት “የዓለምን ህሊና እያናወጠ ነው” ያሉት ቱርክ እስራኤል “በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት (ICJ) ፊት ምላሽ መስጠት ይኖርባታል” ሲሉ ተናግረዋል።
እስራኤል ሀይሎች በጋዛ እያደረጉት ያለው ጥቃት የቀጠሉ ሲሆን በርካታ ሰዎችም ለሞት ተዳርገዋል። የፍልስጤም ሲቪል መከላከያ እንዳለው ከእሁድ ጠዋት ጀምሮ የእስራኤል ጦር በጋዛ በሰነዘረው ጥቃት ከ50 በላይ ህንጻዎች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ገልጿል።
ቃል አቀባዩ ማህሙድ ባሳል እስራኤል ሆን ብላ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ካምፖች አጠገብ ባሉ የመኖሪያ ሕንጻዎች ላይ ጥቃት እየሰነዘረች ነው ሲሉ ከሰዋል። ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ከ200 በላይ ድንኳኖች ወድመዋል ብለዋል።
ዘገባው የአልጀዚራ ነው
በ -ሰላማዊ ወልደገሪማ












