የኢትዮጵያን ባህልና ጥበብን ለተለያዩ የዓለም ሀገራት ለማቅረብ ያለመው የኪን ኢትዮጵያ ዝግጅት በቀጣይ ሁለተኛ ዙሩን በሩሲያ ሊካሄድ መሆኑ ተገለፀ።
ሀገርን ለማስተዋወቅ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ መሰል ፕሮግራም ከ38 አመታት በኋላ እንዲመለስ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
አክለውም ሩሲያ ጋር ያለን ግንኙነት በጥበቡ ዘርፍ ጭምር ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቁመው ግንኙነቱን ለማጠናከር እንደሚረዳ ጠቁመዋል። በሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግና ሞስኮ ከተሞች ዝግጅቱ ከሴፕቴምበር 9 እስከ 11 እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
በተለይም በሞስኮ ከ60 በላይ የሀገራት ሚኒስትሮች በተገኙበት ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ዕድል መገኘቱ ተመላክቷል። የሻኩራ ፕሮዳክሽን ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ ካሙዙ ካሳ ከ30 በላይ ብሄሮችን ባህል ከማሳየት በተጨማሪ የቡና ቅምሻ፣ የፋሽንና ሰርከስ ዝግጅቶች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በቻይና በነበረው የመጀመሪያ ዙር ዝግጅቱ በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ግንኙነትን ማጠናከር ረገድ አበረታች ውጤት የታየበት መሆኑን ገልፀዋል።
ዝግጅቱ በሌሎች ሀገራትም ቀጣይነት የሚኖረው መሆኑ ተመላክቷል።
በ-አብርሃም በለጠ












