ሶስት የተለያዩ የልብ ህመሞችን በሴኮንዶች መለየት የሚችል የመመርመሪያ መሳሪያ ይፋ መሆኑን ተመራማሪዎች ገለፁ፡፡
እ.ኤ.አ.በ1816 በፈረንሳዊው ሐኪም ሬኔ ሌኔክ የተፈለሰፈው ስቴቶስኮፕ (የውስጥ ህመም የመርመሪያ መሳሪያ) ሐኪሞች የታካሚን የሰውነት ውስጣዊ ድምጾችን በተለይም የልብና የሳንባ ድምጽን በማዳመጥ ያጋጠማቸውን ህመም ለመለየት ያስችላቸው የነበረ የዘመኑ አስደናቂ የፈጠራ ውጤት ነበር፡፡
በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ደግሞ የልብ ሐኪም እና በሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ዴቪድ ሊትማን አሁን በመላው አለም በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘውን የስቴቶስኮፕ ንድፍን አበርክቷል፡፡
የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ(AI) ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተሰራው አዲሱ ስቴቶስኮፕ (የውስጥ ህመም መመርመሪያ መሳሪያ) ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ 3 የውስጥ የጤና እክል መለየት ያስችላል ተብሏል።
መገኛውን እንግሊዝ ያደረገው የህክምና ቡድን ዘመናዊውን የመመርመሪያ መሳሪያን በመጠቀም ጥናት ያደረገ ሲሆን የልብ ድካም፣ የልብ ቫልቭ በሽታ እና ያልተለመዱ የልብ ምቶችን በአፋጣኝ ሊለይ እንደሚችል አስታውቀዋል።
የሰው ጆሮ ሊያውቃቸው የማይችሉትን በልብ ምት እና በደም ፍሰት ላይ ያሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን ለመተንተንም ማይክሮፎንን ቴክኖሎጂው ይጠቀማል ተብሏል። የቴክኖሎጂውን ውጤታማነት ለማረጋገጥም ታካሚዎች በነባሩ እና አዲስ የተመረተውን መመርመሪያ መሳሪዎች በመጠቀም እንዲመረሙ መደረጉ ተመላክቷል፡፡
በተደረገው ጥናትም ከ96 ክሊኒኮች የተውጣጡ ከ12,000 በላይ ታካሚዎች በዚህ መሳሪያ ምርመራ እንደተደረገላቸው ሲገለጽ ከ109 ክሊኒኮች የተውጣጡ ሌሎች ታካሚዎች ደግሞ የተለመደውን የመመርመሪያ መሳሪያን በመጠቀም ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡
የኤ አይ ቴክኖሎጂን በታጠቀው መመርመሪያ የተመረመሩ የልብ ድካም ያለባቸው ሰዎች ለአንድ አመት ያህል ሊያውቁት የማይችሉትን ህመማቸውን በ2.33 እጥፍ የማወቅ እድል እንዳላቸው ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።
ምንም ምልክቶች ሳይኖር የስትሮክ አደጋን ሊያስከስትል እና በልዩ የህክምና መሳሪያ ካልተመረመረ ሊገኝ የማይችለው ያልተለመደ የልብ ምት ስርዓትን ደግሞ በ3.5 እጥፍ የበለጠ መለየት አስችሏል፡፡ የልብ ቫልቭ በሽታን ደግሞ በ1.9 እጥፍ የበለጠ ማወቅ ማስቻሉ ተገልጿል፡፡
ዘገባው የ ቢ ቢ ሲ ነው
በ-ሀሴት ሀይሉ












