የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዓባላት ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ሊጥል መሆኑን አስታውቋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከዚህ ቀደም በICC የጣሉት ማዕቀብ ላይ ተጨማሪ አራት አባላትን ማካተታቸውን ተናግረዋል። የትራምፕ አስተዳደር ባለፈው የካቲት ወር የዓለም አቀፉ የወንጀለኝች ፍርድ ቤት ዓባላት ላይ ማዕቀብና የጉዞ እገዳ ማውጣቱ ይታወሳል።
የዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) እስራኤል በጋዛ ከፍተኛ ግፍና የሰብአዊ ቀውስ እየፈፀመች ነው በሚል የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁን ጨምሮ የእስራኤል የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር ዮኻቭ ጋላንት ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱን ተከትሎ ነው በትራምፕ አስተዳደር ማዕቀብ የተጣለበት፤
ሩቢዮ ዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለአሜሪካና ወዳጇ እስራኤል በተቃራኒ የቆመና የደህንነት ስጋት ነው ሲሉም ፈርጀውታል። በዚህም የፍርድቤቱ ተጨማሪ አራት አባላት ላይ ዳግም ማዕቀብ ስለመጣላቸው አሳውቀዋል። ማዕቀብ የተጣለባቸው ውስጥ ሁለቱ ዳኞች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ አቃቢ ህጎች መሆናቸው ታውቋል።
እነዚህ የዓለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት አባላት ከዚህ ቀደም በኔታንያሁ ላይ ከወጣው ክስ እራሳቸውን እንዲያርቁ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከአሜሪካና ከእንግሊዝ ሲደርስባቸው እንደነበር አሳውቀዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማት ድርጊቱን በመኮነን ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።
ዘገባው የአልጀዚራ ነው።
በ-የአብስራ ሚሊዮን












