ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መንግሥት መጽሐፍን አስመልክቶ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ስለ አራቱም ቅጾች ገለጻ አድርገዋል። በገለጻቸውም ካነሷቸው ዋና ነጥቦች መካከል፡-
የመጀመሪያው ቅጽ መደመር የሚለው መጽሐፍ፤ ለመደመር አጠቃላይ እሳቤ መሠረት የሚጥል ነው። የመደመር ጽንሰ ሐሳብ ንድፈ ሐሳባዊ መሠረቱ የተቀመጠው በመጀመሪያው ቅጽ ላይ ነው።
የመጀመሪያው ቅጽ ከሚያነሳቸው ወሳኝ ጥያቄዎች መካከል፤ የሰው ልጅ ፍላጎት ምን ይመስላል፣ ፍላጎቱን ለማሟላት በምን መንገድ ነው ሊራመድ የሚገባው የሚሉት ይጠቀሳሉ። እነዚህን ከሰው ጋር በማስተሳሰር መጽሐፉ በዝርዝር ያነሳል።
ሁለተኛው ቅጽ የሆነው የመደመር መንገድ የተነሱትን ጉዳዮች ደግሞ ሐሳብ፣ ታሪክ፣ ስትራቴጂ በሚሉ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ከፍሎ ማየት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
በመደመር መንገድ ለይተን ካስቀመጥናቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አንዱ በወቅቱ የገጠሙንን ችግሮች በአራት የከፈልንበት ነው። እነሱም የለውጡ ሂደት የመደፈቅ አደጋ ያጋጠመበት፣ የለውጡን ሂደት ጥገናዊ ማድረግ፣ ለውጡን የተቀበሉ በመምሰል ለመጥለፍ የሞከሩ እና ለውጡ ሐቀኛ ሆኖ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣ ማስቻል የሚሉት ናቸው።
ቅጽ ሦስት የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የሚባለውን ያለፉት 100 ዓመታት ታሪክ በአምስት ምድብ በመክፈል የበየነ መሆኑን እና ለዚህም የተጠኑ ባሕርያት መኖራቸውን ያነሳል። በዚህም መሠረት የመጀመሪያው ትውልድ ወግ አጥባቂ፣ ሁለተኛው ትውልድ ህልመኛ፣ ሦስተኛው ትውልድ ውል አልባ፣ አራተኛው ትውልድ ባይተዋር፣ አምስተኛው እና አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ የመደመር ትውልድ ተብለው ተበይነዋል።
ትውልዱ በመደመር እሳቤ እንዴት እንደሚታነጽ በቅጽ ሦስት ተቀምጧል። በተጨማሪም ስለ ጥበብ፣ ውበት፣ ‘ኢሞሽናል ኢንተለጀንስ’፣ ተፈጥሮን በመገንዘብ ተስማምቶ ስለመኖር በዚሁ ቅጽ ተብራርቷል።
አሁን የተሰናዳው አራተኛው ቅጽ የመደመር መንግሥት ይባላል። በዘመናዊት ኢትዮጵያ ያሉ መንግሥታት የመንግሥታቸውን ቅርጽ፣ የመንግሥታቸውን እሳቤ፣ የመንግሥታቸውን አደራረግ በዚህ መንገድ ሠንደው አስቀምጠው አያውቁም።
የመደመር መንግሥት ዋና ሐሳቡ በጽንስ (በንድፍ) ያየነውን መደመር፣ በፍልስፍና ያየነውን መደመር፣ ታሪኩንና ጉዞውን ያየነውን መደመር፣ ትውልድን እንዴት እንደሚሠራ ያየነውን መደመር ተቋማዊ ቅርጽ እንዲይዝ ያደርገዋል።
መንግሥታዊ ቅርጽ እንዲይዝ የሚያደርገው ይህ ሠነድ ነው፤ ሐሳቡ ከግል፣ ከቡድን ወጥቶ እንደ መንግሥት እሳቤው እንዴት እንደሚተገበር በዝርዝር ያስቀምጣል።












