በቱርክ ሰሜን ምዕራብ ክፍል በምትገኘው ባሊኬሲር ግዛት በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 1 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቷል። እሁድ አመሻሽ ላይ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ በርካቶች መቁሰላቸው ተነግሯል ።
የሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ይርሊካያ እንዳስታወቁት፣ በሴንዲርጊ ከተማ በተሰሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የ81 ዓመት አዛውንት ህይወት ማለፉን አረጋግጠዋል ። እንዲሁም በተፈጠረው የመሬት መንቀጥቀጥ 29 ሰዎች ሲቆስሉ አስራ ስድስት ህንፃዎች መፈራረሳቸውን ሚኒሰትሩ ተናግረዋል ።
የቱርክ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኤጀንሲ እንደገለጸው የመሬት መንቀጥቀጡ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 1፡53 ላይ የተከሰተ ሲሆን፣ እስከ ኢስታንቡል ድረስ መሰማቱን አስታውቋል። የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋ በመሬት መንቀጥቀጡ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች በቶሎ እንዲያገግሙ ምኞታቸውን ገልጸዋል ።
ፕሬዝዳንቱ በ X (በቀድሞው ትዊተር) ገጻቸው ላይ፣ “አገራችንን ከማንኛውም ዓይነት አደጋ አምላክ ይጠብቃት” ሲሉም ጽፈዋል። ቱርክ በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የሚያጋጥማት ሲሆን በ2023 7.8 የመጠን መለኪያ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ
ከ53,000 በላይ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉም ይታወሳል ።
ዘገባው የአሶሺየትድ ፕረስ ነው
በ ሰላማዊት ወልደገሪማ












