
የኢትዮጵያ እና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት በንግድ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክም ትብብራቸው የበለጠ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
የ2025 የቻይና የህክምና በጎ ፈቃደኞች የአፍሪካ በጎ አድራጎት ተልዕኮ እና አለም አቀፍ የህክምና በጎ ፈቃደኞች ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሲልክ ሮድ ጠቅላላ ሆስፒታል ተጀምሯል። በመርሃ ግብሩ የተለያዩ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶች፣ የልጆች የልብ ቀዶ ሕክምና፣ የዓይን ሞራ ግርዶሽ፣ የዐይን ህክምና እና የማህፀን ቀዶ ሕክምና እንደሚሰጥ ተመላክቷል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ እንዳሉት፤ የቻይና በጎ ፈቃደኞች ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበው በመርሃ ግብሩ በርካታ ልጆችና ተጨማሪ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ በቻይና በጎ ፈቃደኛ ሀኪሞች የሚካሄደው መርሃ ግብር ከቻይና ህዝቦች ጋር ለዘመናት የቆየ አጋርነት አብሮነት እና የዕድገት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የጤና አገልግሎት ድንበር እንደሌለው ገልጸው፤ የዛሬው መርሃ ግብር ለሁሉም ሰው ጠንካራ መልዕክት እንዳለው ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ እንደተናገሩት፤ ቻይና እና አፍሪካ በቅርብ ጥሩ ወዳጆች፣ አጋሮች እና ወንድማማቾች ናቸው ብለዋል።
የቻይና እና የአፍሪካ የጤና ትብብር ይበልጥ እየጠነከረ መምጣቱን ገልጸው፤ አጋርነታቸውም ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












