በኢትዮጵያ የምግብ ዋጋ መናርን ለመቀነስ እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ካለው የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በተጓዳኝ የ2025 የዓለም የምግብ ዋስትናና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ሁኔታን የተመለከተ ሪፖርት ይፋ ሆኗል። ሪፖርቱ የአየር ንብረት ለውጥና የተለያዩ ግጭቶች የዓለም የምግብ አቅርቦትና ዋጋ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን አመላክቷል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በሪፖርቱ ይፋ ማድረጊያ መርሃግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዓለም ላይ እየጨመረ የመጣው የምግብ እጥረትና የዋጋ መናር የሀገራት የጋራ መፍትሔ ያስፈልገዋል ብለዋል። ችግሩ በተለይም አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን የበለጠ የሚጎዳ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
በልማት ሴፍትኔት መርሃ ግብርም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። የተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሀመድ በበኩላቸው፤ የምግብ ዋጋ እየጨመረ መምጣት በርካታ የዓለም ዜጎች የምግብ ዋስትናቸው እንዳይረጋገጥ ማድረጉን ነው ያነሱት።
በዓለም ላይ ግጭትን ማስቀረት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህ ደግሞ የጋራ ትብብርና ተግባራዊ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) በበበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ የተፈጥሮ አደጋዎችና ግጭት ለጤና አስፈላጊ ምግቦች አቅርቦት ላይ እጥረት ፈጥሯል።
ይህ የምግብ ሥርዓት መዛባት በርካታ ዜጎችን ለጤና እክል ተጋላጭ ማድረጉንም አንስተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












