ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን እየሰራች ነው ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) ገለጹ።
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና በአፍሪካ ኢንቨስትመንት ሴንተር የተዘጋጀው 3ኛው የአፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀመረ።
ኢትዮጵያ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ቀደም ሲል ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ በነበሩት ባንክ፣ ቴሌኮም እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ኢንቨስተሮች እንዲሰማሩ ትልቅ እድል ፈጥሯል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ከመሳብና መሠረተ ልማት ከማስፋፋት ባለፈ መተማመን እና የጋራ እሴትን ማጎልበት ላይ አበክራ እንደምትሰራ አስታውቀዋል።
አፍሪካ ከፍተኛ የሆነ የሰው ሀብት እንዳላት ገልጸው፤ ወጣቶችን በማስተማር እና በማበረታታት የአፍሪካ የቀጣይ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንዲሆኑ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በሌላ በኩል የአፍሪካን የንግድ ትስስር ለማጠናከር፣ ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ እና የእሴት ሰንሰለት ልማትን የማጎልበት ዓለማ የያዘውን አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስትራቴጅ ማጽደቋን አስታውቀዋል።
በፎረሙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የዘርፉ ምሁረን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ኢ ፕ ድ ነው፡፡












