በአዲሱ የትምህርት ዘመን ትምህርት ሚኒስቴር እያስገነባቸው ካሉ ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል የተወሰኑት በመጪው የትምህርት ዘመን ስራ እንደሚጀምሩ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል፡፡
በሳይንስና በቴክኖሎጂ የበቁ የነገ የዚች ሀገር መሪ መሆን የሚችሉ ዜጎችን ለማፍራት የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶቹ ከሁሉም አካባበዎች የሚመጡ ተማሪዎች የሚማሩባቸው፣ አብሮ መኖርና ማደግን የሚለምዱባቸውና የአገሪቱ የወደፊት መሪዎችን የምናፈራባቸው ቦታዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም መነሻ የትምህርት ሚኒስቴር በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች እያስገነባቸው ካሉ ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ድረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል የተወሰኑትን በመጪው የትምህርት ዘመን ስራ ለማስጀመር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ ከአርባ የማያንሱ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተሰጡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናዎች ከሞላ ጎደል ሁሉም ተማሪዎችን ማሳለፍ መቻላቸውንም በአብነት አንስተዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር አዲስ በተገነቡት የፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በ2017 የትምህርት ዘመን 8ኛ ክፍል ካጠናቀቁ ተማሪዎች መካከል መልምሎ ለማስገባት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን፣ ለዚህም ተማሪዎች ተገቢውን መስፈርት አሟልተው እንዲጠባበቁ ማስታወቂያ ማውጣቱ ይታወሳል።












