June 30, 2025
የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና በመላ ኢትዮጵያ በበይነ መረብ እና በወረቀት እየተሰጠ ይገኛል። የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ ፈተናውን በአዲስ አበባ አስጀምረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ እየተሰጠ የሚገኘውን ፈተና በአብርሆት ቤተ መጻህፍት ባስጀመሩበት ውቅት፣ ለፈተናው ተገቢው የቅድመ ዝግጅት ስራ ተሰርቷል ብለዋል ሚኒስቴር ዲኤታዋ። አክለውም፣ ተማሪዎች አዲሱን ስርኣተ ትምህርት መሰረት በማድረግ መጻህፍት አንድ ለአንድ እንዲደርሳቸው መደረጉን፣ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በተዘጋጀበት አግባብም ተገቢውን እውቀት እንዲጨብጡ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

ተማሪዎች በአግባቡ መዘጋጀት እንዲችሉና የሚገባቸውን እውቀት እንዲጨብጡ ለማድረግም ከ400 ሺህ ለሚበልጡ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱንም ነው የገለጹት። መምህራን ትርፍ ጊዜያቸውን ጭምር ተጠቅመው ተማሪዎችን ሲረዱ መቆታቸውን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታ፣ ከመምህራን በተጨማሪ ወላጆችና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችም ተማሪዎችን ሲደግፉና ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
ፈተናው በወረቅትና በበይነ መረብ እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን፣ በተለይ ፈተናው በበይነ መረብ መሰጠቱ ስርቆትና ኩረጃን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ተመላክቷል፡፡ ሚኒስትር ዲኤታዋ ተማሪዎች ፈተናውን በተረጋጋ ሁኑታ እንዲፈተኑና መልካም እድል እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከዛሬ ጀምሮ በሚሰጠው ብሄራዊ ፈተና በአስተዳደሩ 280 ትምህርት ቤቶች 51 ሺ 259 ተማሪዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ አስታውቀዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ከ608 ሺ የሚበልጡ ተማሪዎች በወረቅትና በበይነ መረብ ፈተና እንደሚወሰዱ የጠቆሙት ደግሞ የትምህርት ምዘናና እና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ናቸው።












