ልክ በዚች ቀን ሰኔ 20 1916 ዓ.ም አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ ( አባባ ተስፋዬ) ተወለዱ። በቀድሞው ባሌ ክፍለ ሃገር ልዩ ስሙ ከዱ በተሰኘ ስፍራ ከአባታቸው ኤጀርሳ በዳኔ እና ከእናታቸው ዮንዢ ወርቅ በለጤ የተገኙ የጥበብ ሰው ናቸው፡፡
እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ጎባ ከተማ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ፡፡ ቤተሰባቸው በስራ ምክንያት ወደ ጊንር በመቀየራቸው ትምህርታቸውን በዚያው ቀጠሉ፡፡ ከዚያም ወደ ሐረር ሔደው የፈረንሳዮች ትምህርት ቤት ገብተው ተማሩ፣ ለተወሰኑ ዓመታት ሐረር ከኖሩ በኋላ በ14 ዓመታቸውም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
ተስፋዬ ሳህሉ በጣልያን ወረራ ወቅት በልጅነታቸው ከቤተሰቦቻቸውና ከአካባቢያቸው በቀሰሙት የሽለላ፣ ቀረርቶና መሰል ትውፊታዊ ክዋኔዎች እና በውስጣቸው በነበረው የኪነ ጥበብ ፍቅር እንዲሁም ፍላጎት አማካኝነት ወደ ሙያው ተቀላቀሉ። የአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር ቤት የቴአትር ፍላጎት ያላቸውን ሲያሰባስብ ተስፋዬ ሳህሉ በወር 11 ብር ተከፋይ ተዋናይ ሆኑ።
አባባ ተስፋዬ በትወናው ዓለም ከሰባ በላይ ቴአትሮችን ተጫውተዋል። ሀ ሁ በስድስት ወር፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ ኤዲፐስ ንጉስ፣ አሉላ አባ ነጋ፣ ዳዊትና ኦርዮን፣ ኦቴሎ፣ አስቀያሚዋ ልጃገረድ ፣ ስነ ስቅለት እና የአዛውንቶች አባት ከተወኑባቸው ተውኔቶች ጥቂቶቹ ናቸው።
አባባ ተስፋዬ ስለ ሙያቸው እንዲህ ይሉ ነበር ፤ “ኪነ ጥበብ አባቴ ነው፤ ንጉሤና አሳዳርዬ ነው። እፈራዋለሁ፤ አከብረዋለሁ። የኪነ ጥበብ ባሪያ ነኝ። ከኪነ ጥበብ የምለየው ስሞት ብቻ ነው” በማለት ኪነ ጥበብን ይገልጿታል፡፡
ከ10 በላይ በሚሆኑ ሞያዎችም የተካኑ ነበሩ፡፡ ተዋናይ፣ ድምጻዊ፣ የውዝዋዜ አሰልጣኝ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ፣ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች፣ የልጆች ተረት ደራሲ፣ ተረት ተናጋሪ፣ የዜማና ግጥም ደራሲ፣ የምትሃት ባለሙያ የሚሉት ይጠቀሣሉ። አባባ ተስፋዬ ብዙዎቻችን የምናውቃቸው በልጆች ክፍለ ጊዜ ፕሮግራማቸው ቢሆንም የተለያዩ ሙያ ባለቤትም ነበሩ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ለ36 ዓመታት ያገለገሉት አባባ ተስፋዬ በ1973 ዓ.ም በጡረታ ተገለሉ። ሆኖም በቴአትሩ አይቀጥሉበት እንጂ በልጆች ክፍለ ጊዜ ለረጅም ዓመታት ለአገር እና ለሕዝብ ሠርተዋል።
አባባ ተስፋዬ በሰሯቸው ስራ የተለያዩ ሽልማቶችንም አግኝተዋል፡፡ ከነዚም መካከል የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ የወርቅ ሜዳልያ እና ዩኒየን ሣይቴሽን ከአሜሪካ መንግስት የተቀበሉት ሽልማት ተጠቃሽ ናችው፡፡ በትዳር ሕይወታቸውም ለ48 አመታት አብረው ከኖሩት ከባለቤታቸው ደብሪቱ አይታገድ ጋር ሁለት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ አባባ ተስፋዬ በ 93 አመታቸው ሐምሌ 26 2009 ዓ.ም አርፈዋል፡፡
በ ሔርሜላ ተመስገን












