May 25, 2025
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ኢንስቲቲዩት በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ በህመሙ መያዛቸው ከተጠረጠሩ ታማሚዎች በወሰደው ናሙና በMPox ቫይረስ (በዝንጀሮ ፈንጣጣ) የተያዘ ሰው መገኘቱን አረጋግጧል፡፡ ቫይረሱ የተገኘብት የ21 ቀን እድሜ ያለው ህጻን ሲሆን፣ በተደረገው ምርመራ እናቱም ተጋላጭ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
የህፃኑ አባትም ወደ ጎረቤት ሀገር ሄዶ የነበረ መሆኑ መታወቁና የሄደባቸውን አካባቢዎች እንዲሁም ከግለሰቡ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ግለሰቦችን የመለየትና ክትትል የማድረግ ስራ እንደተጀመረ ይፋ ተደርጓል። ታማሚው ህፃን እና እናቱ፣ አስቀድሞ በተዘጋጀው የለይቶ ማከሚያ፣ ተገቢው የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ የከፋ የጤና እክል አልገጠማቸውም ተብሏል።
የMpox በሽታ (በዝንጀሮ ፈንጣጣ) ቫይረሱ ካለባቸው ግለሰቦች ጋር ንክኪ ያለው ሰው የሚከተሉት ምልክቶች በሚታዩበት ወቅት ማለትም ፦
– ሽፍታ
– ሳል
– ትኩሳት
– የራስ ምታት
– ድካም እና የጀርባ ህመም ሲያስተውል በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ተገቢውን የምርመራና ህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ጥሪ ቀርቧል።












