NBC Ethiopia

ሕገ መንግስት የዜጎችን መብት ለመጠበቅ እና የመንግስትን ስልጣን ለመገደብ የሚያስችል የዜጎች የወል ስምምነት ነው ሲሉ የታሪክ ምሁር የሆኑቱ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ገልጸዋል። ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ማኅበራት ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ግዴታ አለባቸው ብለዋል ።
ፕሮፌሰር ባህሩ ይህ ያሉት በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕገ-መንግሥት እና ሕገ-መንግሥታዊነት በኢትዮጵያ በሚል ለሶስተኛ ጊዜ በተካሄደው የፓርላማ የዜጎች ፎረም ወቅት ነው። በተለያዩ የአለም ሀገራት ተግባራዊ የሆኑ የህገ መንግስት ሰነዶች የወጡበት ዋና አላማና የአፈፃፀም ደረጀ ምን ይመስል እንደነበር የሚያሳይ ጥናታዊ ጹሁፍም አቅርበዋል።
ከዚህ በፊት በኢትዮጵያን ታሪክ የተለያዩ የህገ መንግስት አይነቶች እንደነበሩ ያነሱት የታሪክ ተመራማሪው፤ ህገመንግስት በአንድ በወቅት የሚገኙ ዜጎች የሚያነሷቸውን መሰረታዊ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥያቄዎች መመለስ የማይችል ከሆነ ሊሻሻል የሚችልበት ሁኔታ እንዳለም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ አሁን በስራ ላይ ያለውን ህገ መንግሥት በተመለከተ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ዘንድ የተለያዩ አመለካከቶች እንደሚንጸባረቁ አንስተው፤ ይህንንም ችግር ለመፍታት ቁጭ ብሎ መነጋገር ይገባል ብለዋል። መረጃውን የተወካዮች ም/ቤት ገጽ ነው።













