NBC Ethiopia
ኢትዮጵያ የጀመረችው ብዝኃ ዘርፍ ሪፎርም አረሙን ከስንዴው እየለየ በአስደናቂ የስኬት መንገድ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገራዊ ለውጡን ሰባተኛ ዓመት ስኬታማ ጉዞ እየተከበረ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት “ልህቀት በሰው ተኮር አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል የፌደራል ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ተሞክሮ ተኮር ሥልጠና ዛሬ አስጀምረናል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያውያን የዘመናት መሻት የሆነውን የተሳለጠ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ስርዓት ለመገንባት እና በጽኑ መሠረት ላይ ለማኖር የሚያስችል ሪፎርም እየተካሄደ እንደሚገኝ አመልክተዋል። ሪፎርሙ ለአፍሪካ ተምሳሌት የምትሆን፣ የበለፀገችና ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት እንዲሁም የህዝባችንን የአገልግሎት ፍላጎት ለማርካት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
ይህንን ታሪካዊ ምዕራፍ በማሳካት ዘመን ተሻጋሪና ጠንካራ የመንግሥት የአገልግሎት ሥርዓት ለመዘርጋት ሁሉም የመንግሥት አመራር እና ሰራተኛ በሚጠበቅበት ደረጃ መትጋት እንደሚኖርበት አሳስበዋል። የተሞክሮ ተኮር ስልጠናው የሚካሄደው የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ስርዓትን ለመገንባት በሚያስችሉ በፀደቁ እና በረቂቅ ደረጃ ባሉ ሰነዶች ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሂደቱም እስከ አሁን የሪፎርሙ አፈፃፀም የደረሰበት ደረጃ፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችም ላይ ውይይት እንደሚደረግ ምክትል ጠቅላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ላይ ጠቁመዋል። (ኢዜአ)













