::::::::::::::::::::::::::::::::::::
የጋምቤላ ክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በኦዲት ግኝት ማስመለስ ሂደት የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ደንብና መመሪያ ከማውጣት ጀምሮ የአሰራር ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን ገለጸ።
የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ባለፈው ግማሽ በጀት ዓመት ባካሄደው የፋይናንስ ኦዲት የተሰብሳቢ ሰነድ ክምችት፣ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት እና ተገቢ ያልሆኑ ወጪዎች ግኝትን የተመለከተ ሪፖርት ለክልሉ ምክር ቤት አቅርቧል።
የክልሉ ዋና ኦዲተር ጄኔራል አቶ ኡጁሉ ኡጁሉ የመስሪያ ቤቱን የግማሽ ዓመት የእቅድ ክንውን ሪፖርት ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት የሰነድ ክምችት፣ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ ተገቢ ያልሆኑ ወጪዎች የተገኙት በ36 መስሪያ ቤቶች ላይ በተካሄደ የፋይናንስ ኦዲት ነው።
ከኦዲት ፋይናንስ ግኝቶቹ መካከል ከ113 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የተሰብሳቢ ሰነድ ክምችት፣ ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት መገኘቱን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

እንዲሁም ከ10 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ በተንጠልጣይ ተመዝግቦና ደረሰኝ ሳይቀርብለት ክፍያ ተፈጽሞ የተወራረደ ሰነድ የተገኘ ሲሆን ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ የደመወዝ ተቀናናሽ መዋጮ ፈሰስ ሳይደረግ ተገኝቷል ብለዋል።
በተጨማሪም ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀናሽ የተጨማሪ እሴት ታክስ ፈሰስ ያልተደረጉ ሂሳቦችና 234 ደረሰኞች ለኦዲት ሳይቀርቡ መገኘታቸውንም በሪፖርቱ አመላክተዋል።
መስሪያ ቤቱ ለኦዲት ግኝቶች በሰጠው ግብረ መልስ ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ተመላሽ ማስደረጉን በሪፖርታቸው አብራርተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት የቀረበውን ሪፖርት አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ በግማሽ በጀት ዓመቱ ያከናወናው የኦዲት ግኝት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ግኝቶችን በማስመለስ ረገድ የተከናወኑት ስራዎች በቂ አለመሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይ የኦዲት ግኝቶችን በማስመለስ ረገድ የተጀመሩት ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አቶ ኡጁሉ ኡጁሉ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ አስተያየቶች በሰጡት ማብራሪያ በኦዲት ግኝት ማስመለስ ሂደት የሚታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል ደንብና መመሪያ ከማውጣት ጀምሮ የአሰራር ማሻሻያ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።የክልሉ ምክር ቤት 4ኛ የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዛሬው እለትም ቀጥሎ እያካሄደ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።












