፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 23 2016| NBC ETHIOPIA- የአማራ ክልል ምክር ቤት በሁለተኛ ቀን ውሎው የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅድ እየገመገመ ይገኛል፡፡
በቀረበው እቅድ እንደተገለጸው የግብርናው ዘርፍ ለክልሉ የኢኮኖሚ እድገት ያለውን ድርሻ መሰረት በማድረግ የግብርና ልማቱን በምርምር፣በመስኖ ልማት፣በአፈርና ውሃ ጥበቃ አጠቃቀም ዙሪያ ልዩ ትኩረት ይሰጣል ተብሏል፡፡
ከማህበራዊ ልማት ዘርፍ አንጻርም ዘርፉን ለማሳደግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር ተፈፃሚነቱን ማረጋገጥ ላይ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑም በቀረበው እቅድ ተብራርቷል፡፡
ከመልካም አስተዳደር አንፃርም የህዝብ ደህንነት ለማረጋገጥ የተፈጠረውን የሰላም ችግር በመቀልበስ ክልሉ ወደነበረበት ሰላም እንዲመለስና ልማቱ እንዲረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ተብሏል፡፡
የቀረበው እቅድ ክልሉ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር መልካም ቢሆንም ለተፈጻሚነቱ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የምክር ቤት አባላቱ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በተለይም የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ችግር የክልሉን ህዝብ ለድህነትና ኋላ ቀርነት ዳርጎታል ያሉት የምክር ቤት አባላቱ ትኩረት ከሚስፈልጋቸው አካባቢዎች ላይ ልዩ እቅድ ተይዞ ቢሰራ መልካም ነው ሲሉ አንስተዋል፡፡
የተፈጠረውን የሰላም ችግር ለመፍታት የተቋቋመው የሰላም የምክክር ኮሚቴ ለአማራ ህዝብ ወሳኝ መሆኑን የገለፁ ሲሆን የአማራ ህዝብ ጥያቄ የሆነውን የወሰንና የማንነት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ እንዲያግኝ የክልሉ መንግስት በትኩረት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል፡፡
ለክልሉ ህዝብ ኢኮኖሚ መሰረት የሆነው የግብርና ልማት ዘርፉ ትኩረት ይሻል ያሉት የምክር ቤት አባላቱ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡
የተፈጠረው የኑሮ ውድነት ህዝቡን እየፈተነው መሆኑን ያብራሩት የምክር ቤት አባላቱ የገበያ ማረጋጋት ስራው ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል፡፡ በተለይም ክልሉን በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ ለማድረግ የተጀማመሩ ፕሮጆክቶችንና መሰረተ ልማቶችን ፈጥኖ ማጠናቀቅ ይገባል ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ አረጋ ከበደ በምክር ቤት አባላቱ ለተነሱ ጥቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ክልሉን በኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ ለማሳደግ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንዲሁም ማህበራዊ ልማቶችን አዋህዶ ለመስራት ጥረት እንደሚደረግ ያብራሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይም ለክልሉ ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት የእቅዱ አካል አድርግን አንሰራለን ብለዋል፡፡
ክልሉ በተፈጥሮ ኃብት፣እንሰሳት ሃብትና በሰብል ልማት የታደለ በመሆኑ ይህን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ያሉት ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይም የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የምንችለውን ሁሉ ጥረት አድርገን ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እንሰራን ብለዋል፡፡
በተለይም ዘመናዊ ግብርናን በመከተል ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህ ስኬት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCEthiopiaSC
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












