ካማላ ሃሪስ ማን ናቸው…?
በልጅነት አእምሯቸው ሲሰሙ ያደጉት የአያታቸው የታጋይነት ታሪክ አሁናዊ ማንነታቸው ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው ይነገራል፡፡ ህንዳዊቷ እና ጀማይካዊቷ የአሜሪካ ቁልፍ ዴሞክራት ፖለቲከኛ ሰፊ የማንነት ልዩነት ካላቸው ቤተሰቦች ዝርያቸው ይመዘዛል ፡፡
በአሜሪካን ታሪክ የመጀመሪያ ጥቁር አሜሪካዊ እና እስያ አሜሪካዊት ሴት ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው ካማላ ዴቪ ሃሪስ፡፡በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1964 ወርሃ ጥቅምት በኦክላንድ ካፎርኒያ ነው የተወለዱት ከህንዳዊ እናታቸው Shyamala Gopalan እና ጃማይካዊ አባታቸው Donald J. Harris የተገኙት ካማላ ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅም ናቸው፤ወላጅ እናታቸው ባይሎጂስት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሲሆኑ ወላጅ አባታቸው በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ባለሞያ እና ፕሮፌሰር እንደነበሩ የህይወት ታሪካቸው ያትታል፡፡
ካማላ የሚለው ስያሜያቸውን ያገኙት የሂንዱ እምነት ተከታይ ከሆኑት እናታቸው ሲሆን ስያሜው በሂንዱ እምነት የምትመለከውን እና ብዙ ሴቶች አቅማቸውን እንዲገነቡ ታደርጋለች ብለው ከሚያስቧት ላኪሽ የተሰኘችው ሴት አማልክት የመጣ እንደሆነም ይነገራል፡፡
የሰባት አመት ታዳጊ ሳሉ ወላጆቻቸው በፍቺ መለያየታቸውን ተከትሎ ካማላ እና ታናሽ እህታው ማያ ከወላጅ እናታቸው ጋር ለማደግ ተገደዋል፡፡በልጅነታቸው ጥቁር አሜሪካውያን በቆዳ ቀለማቸው የሚደርስባቸው ግፍ ጭቆና በተወሰነ መጠን በአንድ ወቅት ሰለባ ነበሩ፡፡
ካማላ ሃሪስ ከካሊፎርኒያ የህግ ኮሌጅ የህግ ዲግሪ ከማግኘታቸው አስቀድሞ በዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅም ናቸው፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1990 በተማሩበት የህግ ሞያ የጥብቅና ስራቸውን የጀመሩት ካማላ 2003 የሳን ፍራንሲስኮ አቃቤ ህግ ሆነው አገልግለዋል፡፡ካማላ ሃሪስ ስራቸውን የጀመሩትም የህጻናት እና በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የህግ ጉዳዮ በመያዝ ነበር፡፡
በ2010 በካሊፎርኒያ ግዛት ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ከ4 አመታት በኋላም ዳግም ተመርጠው በግዛቱ ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚ ቦታም ያገለገሉ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት መሆን ችለዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2016 በአሜሪካ ምክር ቤት አባልነት የተመረጡት ካማላ ሃሪስ የዶናልድ ትራምፕ የስደተኞች ፖሊሲ ላይ ጠንከር ባለ ትችት ሲሰነዝሩም ይታወቃሉ፡፡ በተለይም በ2018 የአሜሪካ የጠቅላይ ፍርድቤት እጩ የነበሩትን ብሪት ካቫንጉሀን ጠንከር ባሉ ጥያቄዎቿ መተንፈሻ አሳጥታዋቸው ነበር፡፡ በሳል ፖለቲከኛ እና የዲሞክራቶች ቁልፍ ልጅ መሆናቸውን በአባሎቻቸው እና በህዝብ ፊት አስመስክረዋል፡፡
ካማላ ሃሪስ በአቃቢነት ዘመናቸው ከነበረው የፍቅር ጓደኛቸው ዊሊያም ብራውን በመቀጠል በ2014 በስራ አጋጣሚ የተዋወቁትን ጠበቃ ዳግላስ ኤም ሆፍ ጋር በትዳር በመጣመር የባለቤታቸውን 2 ልጆች በጋራ ያሳድጋሉ እንጅ የአብራክ ክፋይ የላቸውም፡፡
ሃሪስ በ2020ው የአሜሪካ ምርጫ እጩ የነበሩ ሲሆን ነገር ግን በመጀመሪያው ዙር የውድድር ሂደት ላይ እምብዛም የክርክር አፈፃፀሞችን ካሳዩ በኋላ በፍጥነት ደበዘዘዋል፡፡ ዴሞክራቶችን መወከል አልቻሉም ነበር፡፡በተመሳሳይ የምርጫ ዘመን ላይ ለፕሬዘዳንት ሲፎካከሩ የነበሩት ጆ ባይደን ለእርሳቸው የምርጫ ሂደት ሴት የስራ አጋር እንደሚያስፈልጋቸው በመግለፅ ካማላ ሃሪስ ወደፊት እንዲመጡም ሆነዋል፡፡
የእርሳቸው ወደፊት መምጣት ጆባይደን የጥቁር አሜሪካውያንን እንዲሁም የሴት መብት ታጋዮችን ትኩረት ይበልጥ እንዲስቡ እና ስልጣነ መንበሩን እንዲቆናጠጡም በብዙ ደግፏቸዋል፡፡ ወደ ነጩ ቤተመንግስት በመግባት የመጀመሪያዋ ጥቁር አሜሪካዊት ሴት፤እንዲሁም እስያዊ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን የመጀመሪያዋ የሚሉ ማዕረጎችን የማግኘት ታሪክ ሰርተዋል፡፡













