፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 09 2016| NBC ETHIOPIA-“ሠላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሠላም” በሚል መሪ ቃል በባህር ዳር ከተማ በቀበሌዎችና ክፍለ ከተሞች ደረጃ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ኮንፍረንስ የማጠቃለያ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የባህር ዳር ከተማን ሠላም ከማስከበር በተጓዳኝ ለነዋሪዎች፣ ለጎብኝዎችና ለባለሀብቶች ምቹ ለማድረግ የስማርት ባህርዳር ፕሮጀክት እየተተገበረ እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ገልጸዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አቶ ጎሹ እንዳላማው እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የከተማዋንና የአካባቢውን ሠላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ለልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል።
በዚህም ከተማዋን በሀገር አቀፍ፣ በአህጉርና በዓለም ተወዳዳሪ ለማድረግ የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት እየተተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።በጥናት ላይ በመመስረት በከተማዋ ዋና ዋና አደባባዮችና ገዥ ቦታዎች ላይ የ”ሲሲ ቲቪ” ካሜራ ተከላና የመቆጣጠሪያ ማዕከል የማቋቋም ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በተጨማሪም በስድስት ክፍለ ከተሞች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የመረጃ ስርዓት በማገናኘት የደንበኞችን የመረጃ አያያዝ ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም ከ100 ሺህ በላይ ፋይሎችን ወደ ሲስተም ማስገባት መቻሉን ጠቁመው፤ ይህም በመረጃ ማጥፋት የሚፈጠር የመልካም አስተዳደር ችግርን ለማቃለል እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የመንገድ መሰረተ ልማት፣ የአረንጓዴ አሻራና ሌሎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች አበረታች ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል።የልማት ስራዎችን ማከናወን የተቻለውም ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር መሆኑን ተናግረዋል።የዛሬው ውይይትም የተገኘውን ሠላም በማፅናት የላቀ ልማት ለማስመዝገብ የሠላም ካውንስሉ ያቀረበውን የውይይት ሃሳብ እንዲሳካ ህብረተሰቡ ሚናውን እንዲጫወት ለማስቻል በማለም ነው ብለዋል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCEthiopiaSC
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Website – https://nbcethiopia.com/news/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv











