፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 25 2016| NBC ETHIOPIA-ባነሳው ፎቶግራፍ አለም ላይ ላይረሳ ታሪኩ ተከትቧል፤ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ 1994 ፑሊትዘር የተሰኘ ሸላሚ ድርጅት፤ ፎቶግራፍ ማንሳትስ እንዲህ ሲል ሸልሞታል፡፡ ይህም ሳይንስ የአለም መገናኛ ብዙሀን ጋዜጠኝነት ይህ ነው ሲሉ ያነሳውን ፎቶግራፍ የጥበበኛ አይን በማለት ተቀባብለው ሲያበቃ እርሱ ግን ጉዞው ሞት ሆኗል-ኬቨን ካርተር
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1960 በወረሀ መስከረም በደቡብ አፍሪካዊቷ መዲና ጆሃንስበርግ፤ የአፓርታይድ ስርዓት በተንሰራፋባት ደቡብ አፍሪካ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች ተወለደ፡፡
ኬቨን በእድገቱ በአከባቢው የሚፈጸመውን የጥቁሮች በደል እና በገዛ ሀገራቸው የሚፈጸምባቸውን ግፍ ተመልክቷል፡፡ ይህ ኬቨን ግፍን ተቃዋሚ እንዲሆን አድርጎታል፡፡የሚከታተለውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በማቋረጥ የፋርማሲ ትምህርትን በመከታተል ሞያዊ አበርክቶ ለማድረግ ውትድርናን ተቀላቅሏል፡፡
ከእግረኛ ወታደርነት በመተውም ለአራት አመታት ወዳገለገለበት አየር ሃይል ተቀላቅሏል፡፡በፈረንጆቹ 1980 በአንድ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በጥቁር አስተናጋጅ ላይ ሲደረግ የተመለከተውን ግፍ በመቃወሙ ክፉኛ ድብደባ ደርሶበት ከስራ ገበታውም እንዲሰናበት ሆኗል፡፡
ከዚም በኋላ ነበር በአለም አቀፍ ደረጃ እስካሁንም ድረስ መነጋገሪያ ወደሆነበት እና ላይረሳ ስሙ በታሪክ መዝገብ የተጻፈበት ሞያን የተቀላቀለው፤እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1983 በፕሪቶሪያ በሚገኝ አንድ በቤተክርስቲያን አካባቢ የተፈጠረውን የቦንብ ጥቃት ባየበት ማግስት የፎቶግራፍ እና የጋዜጠኝነት ስራን ተያያዘው፡፡
በስፖርት የፎቶግራፍ ጋዜጠኝነት ስራውን ሀ ብሎ የጀመረው ኬቨን በ1984 ወደ ጆሃስበርግ በመዘዋወር ለአፓርታይድ ጭካኔ የተጋለጡ ዜጎችን ጉዳት በሚያሳዩ ፎቶግራፎች ስራውን ጀምሯል፡፡

በፈረንጆቹ ወርሀ መጋቢት 1993 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኦፕሬሽን ላይፍላይን ሱዳን ዘመቻ ጆአዎ ሲልቫ ለተሠኘው ጋዜጠኛ በደቡብ ሱዳን ስላለው ረሃብ ፤የእርስ በርስ ጦርነት እንዲዘግብ እድል ሰጠው፡፡
ፎቶግረፈሩ ሲልቫም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ስራውን እንዲያሰፋበት እና ለሌሎች የእድል በሮች መከፈት ይጠቅምህ ይሆናል ሲል ለካርተር ነገረው፡፡ይህንን እድል ያለማቅማማት የተቀበለው ኬን ጉዞውን ወደ ሱዳን አደረገ፤ ከመጀመሪያ መዳረሻ አንስቶ የተመለከተው ግፍ፣ ስቃይና መገዳደል ሲያስታውስ ከአይምሮው በላይ ሆኖበት እንደነበር በተደጋጋሚ ይናገራል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች በደቡብ ሱዳን ከሚገኘው አማጺ ቡድን ባገኙት ፍቃድ መሰረት ምግብ ለማድረስ ከተጓዙት ሰራተኞች ጋር ካርተር አስከፊ ረሃብ ወደ ተከሰተበት ስፍራ አቀና፤ በስፍራው ከመንግስታቱ ድርጅት ሰራተኞች ምግብ ለመቀበል በርሀብ ብዛት አቅም ያነሳቸው ብዙዎች ጉልበታቸውን እንደፈቀደ መሯሯጥ ጀመሩ፤የቻሉ ወዳካባቢው ይገሰግሳሉ አንዳንዶች ግን በከፍተኛው ረሃብ ምክንያት ምግብ የሚሰጥበት ስፍራም ሳይደርሱ በመንገድ ወድቀው ይቀራሉ፡፡
ከባዱ ረሃብ ካዳከማቸው መካከል ካርተር በካሜራው ያስቀራት ህጻን አንዷ ናት፤ህጻኗ እናቷ ጥላት ወደሄደችበት የምግብ ማደያ ስፍራ ለመጓዝ በነበረችበት ሁነት ላይ ረሀብ አንጀቷን አጣብቋት መንገድ መቀጠል አቅቷታል፤ ጥንባንሳው ከርሷ ቅርብ እርቀት ቆሞ ነፍሷ ወጥቶለት ለመብላት ቋምጦ ይጠባበቃታል፤ ይህ ሂደት በካሜራው ምስልን ከስቷል፡፡
ወደ ስፍራው በማቅናት ላይ ሳለ ይህንን ሁነት የተመለከተው ፎቶግራፍ ጋዜጠኛ ካርተር የጥንባንሳውን ሁኔታ እና የልጅቷን ነፍስ ውጪ ነፍስ ጊቢ ሁነት ችግሩን በሰፊው ሊገልፅ በሚችል መልኩ በካሜራው በማስቀረት ለኒውዮርክ ታይምስ ምስሉን ሸጠው፡፡ቀናት አለፉ ምስሉ በኒውዮርክ ታይምስ ፊት ገፅ ከወጣ በኋላ በርካቶች ጥያቄን ማንሳት ጀመሩ፤ ከዚህም ከዛም ምስሉስ ተነሳ ህጻኗ የት ደረሰች የሚል የሞራል ጥያቄን አቀረቡ፤ ተዋቂው ኒውዮርክ ታይምስም ፎቶግራፈር ካርተርን ይህውና የፎቶው ባለቤት ሲል ካርተርን አጋፈጠ፤ፎቶግራፈሩ ካርተር ልጅቷን በዛ ሁኔታ ውስጥ ካነሳው በኋላ እንዳላያት እና ምንም እርዳታ ሳያረግላት ካካባቢው መራቁን ፤ አሁን የት እንደምትገኝ እንደማያውቅ ተናገረ፡፡
ማጉረምረም በዛ ይህ ምን ዓይነት ጭካኔ ነውም ተባለ፤ በተቃራኒው ያሉ ደግሞ በሱዳን የሚገኘውን ሰቆቃ በትክክል የሚገልጽ ሲሉ አሞካሹት፤ በፎቶግራፍ የእይታው ጥበብ ተደነቁ በፊውቸር ፎቶግራፍ ዘርፍ የፑሊትዘር ሽልማት አሸናፊም ሆነ፤
ነገር ግን ጩሀቱ አልበረደም ነበር፤ ልጅቷስ? ልጅቷስ? የሚል ጩሀት…መልስ የለም ካርተርም ከሰዎች ከሚደርስበት መጥፎ አስተያየት እና ጥያቄ ባሻገር ከራሱ የህሊና ጥያቄ ማምለጥ ከበደው ተቸገረ፤ አልቻለም ታመመ ፤ጭንቀት ውስጥ ገባ በመጨረሻም ብጫቂ ወረቀት ጻፈ እራሱን አጥፍቶ ተገኘ…ሸልመው ወደ ሞት ሸኙት….በተወለደ በ 33 አመቱ ሀምሌ 1994 ከዚህ አለም በሞት ተለየ ሲል ታሪክ ለዝክር አስቀመጠው፡፡

በርሱ የህይወት ታሪክ ዙሪያ የሚያትት መፅሀፍ ተጻፈ የፎቶግራፍ ግሩፕ አባል በነበረበት ባንግ ብንግ ክለብ ርዕስ ተሰጥቶት ታተመ፤ በህይወቱ ዙሪያ የሚያትት ፊልም ወጣ፤ከነዚህ ሁሉ በኋላ በፈረንጆቹ 2011 ነበር መጀመሪያ ጊዜ በምስሉ ላይ ያለችው ህጻን ወላጅ አባት ነኝ ያለ ግለሰብ ከረዥም አመታት በኋላ የብዙዎችን ጥያቄ የመለሰው፤ በምስሉ ላይ ያለው ህጻን ወንድ እንደሆነ እና ልጁ በወቅቱ ወዲያው ህይወቱ እንዳላለፈ እና እርዳታ የመስጫ ድርጅቱ ጋር ደርሶ እርዳታ እንደተደረገለት፤ ነገር ግን ከ 4 አመት በኋላ በትኩሳት ህይወቱ እንዳለፈ ተናገረ ነገር ግን የፎቶግራፈሩ እና ጋዜጠኛ ካርተር ህይወት ላይመለስ ተሰናብቷል፤ ካርተር የለም ታሪኩ እንጂ፡፡












