፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 21 2016| NBC ETHIOPIA- የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም እ.ኤ.አ. 2024 የዓለማችን ለጉዞ እና ለቱሪዝም ምርጥ መዳረሻ የሆኑ ሀገራትን ይፋ አድርጓል፡፡ ለጎብኚዎች የተሞሉ መሠረተ ልማትን ማሟላት፣ የጉዞ ፍሰት፣ የታደሉት የተፈጥሮ ገጸ በረከቶቻቸው፣ ጥራታቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣አየር መንገዶች እንዲሁም በቂ የሰው ኃይል አቅርቦት ፎረሙ ለሀገራቱ ደረጃ የሰጠበት መስፈርቶች ናቸው፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ ከሚገኙት 10 ምርጥ ሀገራት ውስጥ ስድስቱ መገኛቸውን በአውሮፓ ነው ይላል ሪፖርቱ፡፡
አውስትራሊያ

አውስትራሊያ አስደናቂ የተፈጥሮ ገጸ በረከቶች ፣ የመድብለ ባህላዊ ማህበረሰቦች፣ተወዳጅ ምግብ እና መጠጥ፣ ለሁሉ ተስማሚ የሆነ የአየር ሁኔታ የተላበሰች ሀገር በመሆኗ ብዙዎች መዳረሻ ያደርጋታል፡፡ ተቋሙ ይፋ ባደረገው የቱሪስት መዳረሻ ሀገራት መካከል የ5ተኛ ደረጃን አግኝታለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ 2023 7.3 ሚሊዮን ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች መቀበል የቻለች ሀገርን እንደሆነች በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ በተያዘው ፈረንጆቹ አመት ወደ ሀገሪቷ የሚመጡ የቱሪስት ብዛት 9.3 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል፡፡
ፈረንሳይ

ፈረንሳይ ለተዝናኖት እጅግ ተመራጭ እና አስደናቂ ከሆኑ አገሮች አንዷ ነች። ለአይን ማራኪ የሆኑ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ቦታዎች፣ እድሜ ጠገብ ሕንፃዎች፣ ግርማ ሞገስ የተላበሱ ቤተመንግስቶች እንዲሁም ጸጥ ያሉ የባህር ዳርቻዎችን የተላበሰች ሀገር ናት፡፡ ሀገሪቷ ተፈጥሮ ካደለቻት መስህቦች እንዲሁም የምታዘጋጃቸው አለም አቀፍ መሰናዶዎች በሁሉም ልብ ውስጥ እንድትቀር አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2010 ጀምሮ ፈረንሳይ በየዓመቱ በአማካይ 77.8 ሚሊዮን ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ስታስተናግድ የቆየች ሲሆን በ2022 79.4 ሚሊዮን ጎብኚዎችን ለተዝናኖት መርጠዋታል፡፡ በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ሀገሪቷ በቱሪስቶች ዘንድ ያላትን ተመራጭነትን እንዲሁም የቀረበውን መስፈርቶች በማላላት የ4ተኛነት ደረጃን ሰጥቷታል፡፡
ጃፓን

የኮቪድ 19 መጥፋቱን ተከትሎ በጃፓን የኢኮኖሚ እና የቱሪስት መዳረሻዎች እንደ አዲስ ማንሰራራት ጀምረዋል፡፡ በ2024 የአለም አቀፍ የቱሪዝም እድገት ከሌሎቹ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር በመዘግየቱ ጎብኚዎች ወደ ኤዥያ ማቅናት ጀምረዋል፡፡ ሀገሪቷ ከአመታት በኋላ እያሳየችው ባለው እድገት በዓለም ሶስተኛዋ የቱሪስት መዳረሻ መሆን ችላለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2024 በወር ብቻ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወደ ጃፓን ተጉዘዋል፡፡ በመጪው የበጋ በዓላት ተጨማሪ ጎብኚዎች ሀገሪቷን በመዳረሻነት እንደሚመርጧት ከወዲሁ እንደሚጎበኙ ይጠበቃል። ዋና ከተማዋ ቶኪዮ እውቅ የጉዞ መዳረሻዎች የሞሉባት ስትሆን የጃፓን የንግድ ማዕከል እና ልዩ የባህል ምግቦች እና የጥንታዊ ስፍራዎች መነሀሪያ ናት፡፡ ስፔን

በአውሮፓ የጉዞ መልህቅ በማለት ሪፖርቱ የሰየማት ሀገር "ከፍተኛ ቱሪስት ፍሰት ያለባት እንዲሁም የብዙሀን መድረሻ ባለቤት" ድርብ ዝናን መጎናጸፍ ችላለች፡፡ ስፔን እ.ኤ.አ. በ2023 85.1 ሚሊዮን አለም አቀፍ ቱሪስቶችን አስተናግዳለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ 2024 የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ብቻ ከ 16 ሚሊዮን በላይ የውጭ አገር ጎብኚዎች የስፔንን ምድር ረግጠዋል፡፡ ካለፈው ዓመት ጋርም ሲነጻጸርም በ17 በመቶ ብልጫ አለው። ለዚህም ይመስላል ተቋሙ 2024 2ተኛዋ የ2024 የዓለማችን የጉዞ እና የቱሪዝም ምርጥ መዳረሻ ያላት፡፡ አሜሪካ

የዓለማችን ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት አሜሪካ በቱሪስት መዳረሻዎቿ የቀዳሚውን ስፍራ መቆናጠጥ ችላለች፡፡ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የ2024 የዓለማችን የጉዞ እና የቱሪዝም ምርጥ ሀገር በማለትም ሰይሟታል፡፡ በሪፖርቱ "የብዙዎች" መድረሻ የተባለችው አሜሪካ ከአየር መንገዷ ጀምሮ እስከ አስጎብኚዎች እና ጎብኚዎችን በተገቢው መልኩ ማስተናገድን ጨምሮ ተቋሙ ያወጣቸውን መስፈርቶች አሟልታለች ይላል ሪፖርቱ፡፡
እንደ ኒውዮርክ ፣ ሎስ አንጀለስ፣ አትላንታ፣ ላስ ቬጋስ፣ ኒው ኦርሊንስ፣ ቺካጎ፣ ያሉት ከተሞቿ ለቱሪስት መዳረሻ ከሆኑ ግዛቶች መካከል በዋነኝንት ተጠቅሰዋል፡፡ የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ጎብኚዎች ቁጥር አመት አመት እየጨመረ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ ከ2021 እስከ 2022 ወደ አሜሪካ የሚገቡ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ በ2021 22.28 ሚሊዮን ሰዎች ለተዝናኖት አሜሪካንን መዳረሻቸው ያደረጉ ሲሆን በ2022 50.87 ሚሊዮን ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ወደ አሜሪካ አስደሳች የእረፍት ጊዜን ለማሳለች አምርተዋል፡:ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ቻይና፣ ጣሊያን እና ስዊዘርላንድ በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ከ6 እስከ 10 በቅደም ተከትል የአመቱ የዓለም ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ በሚል የሰየማቸው ሀገራት ናቸው፡፡












