፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሚያዚያ 30 2016| NBC ETHIOPIA- እንደ ፓሪስ፣ ለንደን ወይም ሮም ካሉ ከተሞች ያልተናነሰ ልዩ ባህል፣ታሪካዊ እና የስነ-ህንፃ ስፍራዎች መገኛ የሆኑ ከተሞች በርካታ ናቸው፡፡ ከተሞቹ ትኩረት ቢያገኙ የበርካታ ጎብኝዎችን ቀልብ መሳብ የሚችሉ መዳረሻዎች አሏቸው፡፡
ቫልፓራይሶ፣ ቺሊ
ቫልፓራይሶ ከዋና ከተማዋ ሳንቲያጎ በስተምዕራብ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በቺሊ ማዕከላዊ የባህር ዳርቻ ላይ የምትገኝ የወደብ ከተማ ናት፡፡

ይች ብዙም የማትታወቅ ከተማ ብዙ ሊጎበኙ የሚችሉ ነገሮች መገኛ ናት፡፡ አስደናቂ አቀማመጥ ያላቸው ኮረብታዎቿ፤ ታሪካዊ አርክቴክቶቿ፣ መንገዶቿ እና ፓስፊክ ውቅያኖስን ለመመልከት ምቹ የሆኑ ስፍራዎቿ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ቫልፓራይሶ በስነ-ህንፃ ኪነጥበብ ያሸበረቀች በመሆኗ ታሪካዊ ማዕከል ልትሆን በቅታለች፡፡ በዚህም በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት እንድትመዘገብ ሆኗል፡፡ ብዙ ሕዝብ የሚበዛባቸው ኮረብታዎቿ እና ጥንታዊ አሳንሰሮቿ የከተማዋ ሌላኛው መገለጫዋ ነው፡፡ የተለያዩ ቀለም ያላቸው ህንጻዎች፤ መኖሪያ ቤቶች፤ መንግስት ተቋማት እና ሆቴሎች ጥሩ የጎብኚ መዳረሻ ስፍራዎች ናቸው፡፡ ታሪካዊው የቫልፓራሶ አውራጃ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የኪነ ህንጻ ጥበብ ማሳያ ነው፡፡
በቫልፓራይሶ ከተማ በሚገኙ ህንጻዎች ግድግዳ ላይ በሀገር ውስጥ እና በአለም አቀፍ የጎዳና ላይ አርቲስቶች የጥበብ ስራዎች ተሸፍኗል፣ይህም ከአለም ታላላቅ የጎዳና ጥበብ ከሚገኝባቸው ከተሞች አንዷ እንድትሆን አድርጓታል፡፡
ቪልኒየስ, ሊቱዌኒያ
ቪልኒየስ የሊትዌኒያ ዋና ከተማ ናት ፣ በሰሜን አውሮፓ የምትገኝ ከተማ ብትሆንም እንዳላት ታሪካዊ ጥንታዊ እና አስደናቂ መልከአ ምድር በቂ ትኩረት ያላገኘች ከተማ ናት፡፡

ከተማዋ እንደ ፓሪስ፣ ለንደን ወይም ሮም ካሉ የአውሮፓ ዋና ከተሞች ጋር ባትወዳደርም ነገር ግን ቪልኒየስ ከሀገራቱ እኩል ያልተናነሰ ታሪክ፣ ባህል እና ድንቅ መልክአ ምድሮች መገኛ ናት፡፡
ጥንታዊ ስፍራ እና ታሪካዊ ቦታዎች፤ ከተማዋን ከጥግ እስከ ጥግ ማያ ማማ እስከ ልዩ ልዩ የጥበብ ማሳያ ህንጻዎች፤ በትላልቅ ስፍራ ላይ የተገነቡ ንጹ አየር መውሰጃ እና መዝናኛ ስፍራዎች እስከ በ15ተኛው በ16 ተኛው እና በ17ኛው ክፍለዘመን የተገነቡ የባህል ማዕከላት እና የመንግስት አስተዳደር ተቋማት መገለጫዎቿ ናቸው፡፡
ጥንታዊነትን ከዘመናዊነት ጋር አጣምራ በያዘችው በዝች ከተማ 326 ነጥብ 5 ሜትር የሚረዝመውን የቪልኒየስ ቴሌቪዥን ታወርን፤ቪልኒየስ ካቴድራል፤በ14ተኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው ገዲሚናስ ታወር፤ ከከተማዋ 17 ኪሊሜትር እርቀት ላይ የምትገኛዋን ኢሩፖስ ፓርካስ፤ወደ ከተማዋ የሚያቀኑ ቱሪስቶች እንዲጎበኙት ይመከራል፡፡
የቪልኒየስ ኦልድ ታውን የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ስፍራ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ጠባብ ጠመዝማዛ መንገዶች፤ በቀለማት ያሸበረቁ ሕንፃዎች እና በርካታ ታሪካዊ ሐውልቶች ከተማዋ ሌላ ውበት ናቸው፡፡
ግዳንስክ፣ ፖላንድ
ግዳንስክ በፖላንድ ሰሜናዊ የባህር ዳርቻ ላይ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ይህች ከተማ ብዙም ጎብኝዎች የማያቀኑባት ነገር ግን ለጉብኝት ቢሄዱባት ተደስተው ተዝናንተው የሚመለሱባት ከተማ ናት፡፡

ይች ታሪካዊ የወደብ ከተማ በታሪክ የበለጸገች እና አስደናቂ ባህል ያላት ከተማ በመሆኗ ከተማዋን መገሆብኘት የሚያስቆጭ አይደለም፡፡
ባለፉት ዘመናት ጀርመን እና ሩሲያን ጨምሮ ከተማዋ በተለያዩ ሀገራት ስትትተዳደር ቆይታለች፡፡
በዚህም የሌሎች አገራት ባህል እና የስነ ህንጻ ጥበብ ከተማዋን ሌላ ገፅታ ሰቷታል፡፡ ለአይን በሚማርኩ ህንጻዎች መካከል የሚያቋርጡ ወንዞች፤ በደማቅ ቀለም ያሸበረቁ የመኖሪያ መንደሮች፤ የመዝናኛ ስፍራዎች፤ ተደርድረው የተገነቡ ተቋማት የከተማዋ ድምቀት ናቸው፡፡
ከከተማዋ ጥግ የሚገኘው የሄቪ-ሊያነም ሴንተር እና ሳይንስ ሙዚየም፣ በማዕከላዊ አደባባይ የሚገኘው አርተስ ፍርድ ቤት እና አስደናቂ የፖላንድ ጥበብ እና ቅርሶች ስብስብን የያዘው የግዳንስክ ብሔራዊ ሙዚየም ጎብኚዎችን ወደ ቀድሞው ዘመን አሻግረው እንዲመለከቱ የሚያስችል ስፍራ ነው፡፡












