፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሚያዚያ 21 2016| NBC ETHIOPIA-ቴክኖሎጂ በእያንዳንዱ የህይወታችን እንቅስቃሴ ውስጥ ያለው ሚና እያደገ ብሎም ያለ ቴክኖሎጂ ሕይወትን ማሰብ የሚከብድበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ዘመን ካፈራቸው ቴክኖሎጂዎች መካከል አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ(ሰውሰራሽ አስተውሎት) አንዱ ሲሆን ተጽእኖው በተለያዩ ዘርፎች ጎልቶ እየታየ ይገኛል፡፡ በፈረንጆቹ ህዳር 2022 በ open AI ኩባንያ አማካኝነት የተፈጠረው ቻት ጂፒቲ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ወደ አዲስ ስርዓት የለወጠ ተብሎለታል፡፡ ይህንን ተከትሎም ትላልቅ የአለማችን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አዳዲስ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስተዋወቅ የፉክክር ሜዳውን ተቀላቅለዋል፡

ቻት ጂፒቲ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ዉጤት ሲሆን ሰዎች የፈለጉትን ጥያቄ በመፃፍ ለጥያቄያቸዉ ፈጣንና ቅልብጭ ባለ መንገድ የተለያዩ መረጃዎችን ቃኝቶ ምላሽ የሚሰጥ የቴክኖሎጂ ዉጤት ነዉ፡፡ ቻት ጂፒቲ ከ2021 በፊት ያሉ የጋዜጣና መጽሄት፤ የጥናትና ምርምር፤ መጽሀፍትና የሰዉ ልጅ ማወቅ የሚፈልጋቸዉን ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ምላሽ የሚሰጥ ነዉ፡፡ ይህ የቴክኖሎጂ ዉጤት በተጠየቀበት ዉስን ደቂቃዎች ዉስጥ እስከ 25000 ቃላት ድረስ በመጠቀም ለተጠየቀዉ ጉዳይ ዝርዝር መረጃዎችን በቀላል አቀራረብ ምላሽ ይሰጣል፡፡ መተግበሪያው አገልግሎት ላይ በዋለ 1 ሳምንት ውስጥ ከ 1 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን ማፍራት የቻለ ሲሆን በአሁኑ ሰአት ከ 180 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት በቅርቡ የወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡ ይህ መተግበሪያ በየካቲት 2024 ከ 1.6 ቢሊዮን በላይ ጎብኜዎችን አግኝቷል፡፡
የኢንተርኔት ዓለሙን በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቆጣጠረው ቻትጂፒቲ በርካቶች አዲሱን አገልግሎት አማራጭ አድርገው መጠቀማቸውን ተከትሎ የጎግል ኩባንያ ጎግል ጄሚኒ የተሰኘ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሞደሌን በፈረንጆቹ ታህሳስ 2023 ለተጠቃሚዎች እንካችሁ ብሏል፡፡
ከተዋወቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በAI ተጠቃሚዎች ዘንድ ተፈላጊነቱ የጨመረው ጀሚኒ እስከዛሬ ከነበሩት ትልቁ እና አቅም ያለው ሞዴል መሆኑን ኩባንያው አስታውቋል፡፡

Google Gemini እንደ OpenAI GPT ያለ የአርቴፊሻል አስተውሎት ሞዴል ቢሆንም ምስሎችን፣ ኦዲዮዎችን፣ ቪዲዮዎች እና ሌሎች መረጃዎችን ከሌሎች በተሻለ መረዳት እና መስራት ብሎም ማጣመር ይችላል። ውስብስብ ጥያቄና መረጃን ለሚጠይቁ ተጠቃሚዎችም ተጨማሪ ምላሽ ይሰጣል፡፡ እንዲሁም በስማርት ስልክ ጨምሮ በሎሎችም በብቃት መስራት እንዲችል ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡
የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በአሁኑ ሰአት በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ውድድር ጀምረዋል፡፡በዚህም የተነሳ አብዛኛዎቹ ኩባንያዎች ሞዴሎቻቸው እንዴት እንደሚሰሩ እና እንደሚለያዩ በዝርዝር ከመግለፅ ይቆጠባሉ፡፡ ከሰሞኑም የፌስቡክ ፤ኢንስታግራም ዋት አፕ ባለቤት የሆነው ሜታ ኩባንያ አዲስ ሜታ ቻት ቦት የተሰኘ አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ ሞዴል አስተዋውቋል፡፡ Meta AI የሜታ ቻት ጂፒቲ ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረቡን ነው የተገለፀው፡፡ ከዚ በኃላ በፌስቡክ ቻት ማደረግና ፖስት ከመመለክት በዘለለ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መስጠት ማግኘት የሚችሉበት መሆኑን የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙከንበርግ ገልፃል፡፡

Meta AI በዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም፣ ሜሴንጀር፣ ፌስቡክ በቻት ውስጥ “@meta ai” በመፃፍ ማግኘት ይቻላል ሲል ኩባንያው አስታውቋል፡፡
ሜታ ኩባንያ አዲስ የራሱን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ማስተዋወቄ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት የገቡበትን ውድድር የሚያመላክት ነው ተብሏል፡፡ ሜታ ይፋ ያደረገው ሰው ሰራሽ አስተውሎት ባዘዙት መሰረት ጥያቄዎችዎን ይመልሳል፣ ጽሁፍን ወደ ምስል መቀየር እንዲሁም እጅግ የተወሳሰቡ ስራዎችን ይሰራል ሲል ኩባንያው አስታውቋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ “በነጻነት ሊጠቀሙበት የሚችሉት እጅግ በጣም ረቂቅ AI ረዳት” ሲል ገልፆታል፡፡ የሜታ አዲሱ አርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ በአሁኑ ሰአት በአሜሪካ ብቻ የተለቀቀ ሲሆን በቀን 3 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳለው እየተነገረ ነው። በቀጣይ በአውስትራሊያ ፣ ካናዳ ፣ ጋና ፣ ጃማይካ ፣ ማላዊ ፣ ኒውዝላንድ እና ናይጄሪያ እንዲሁም በተመረጡ ሌሎች ስድስት ሀገራት ይለቀቃል ተብላል፡፡












