አዲስ አበባ | ሚያዚያ 04፣ 2016| NBC ETHIOPIA-በሀገራችን የራስን ጤና በመጠበቅ እና በመከታተል ረገድ ብዙ ጉድለቶች ቢኖሩም የአእምሮን ጤና ደሞ ከሌሎች አካላቶች ጤና በላይ ትኩረት ሲነፈገው እንመለከታለን። እንዲሁም የአእምሮ ጤና እክሎችን ከሌሎች አካላት በተለየ በመንፈሳዊ መንገድ በመረዳት ተገቢው የህክምና ክትትል ሳይደረግ ሲቀር እናያለን።
ከዚህም በተጨማሪ የአእምሮ ህሙማን መጥፎ ስያሜዎች ሲሰጧቸው እና ለአካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳቶች ሲጋለጡ መመልከት የተለመደ ነው። ዛሬ ከአእምሮ ህመሞች መሃል አንዱ የሆነውን ስኪዞፈሪንያን(በገሀዱ አለም የማይታዩ እና የማይሰሙ ነገሮችን የማየት እና የመስማት ህመም) በጥቂቱ እንመልከት።
ስኪዞፈሪንያ ምንድነው?

ስኪዞፈሪንያ ጤናማ ሰዎች ከሚሰማቸው ስሜት ባፈነገጠ መልኩ የሚፈራረቅ የስሜት መጋነን እና መቀዛቀዝ እንዲሁም ከእውነታ ውጪ የሆኑ አስተውሎቶችን እና አመለካከቶችን የሚያመጣ የአእምሮ ህመም ነው።
አንድ በመቶ ወይም ከዚያ በታች የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚያጠቃ ሲሆን በቤተሰብ ውስጥ ከዚህ በፊት የስኪዞፍሬኒያ ታማሚ ካለ ግን ይህ ቁጥር ወደ አስር በመቶ ከፍ ይላል።ስለዚህ ስኪዞፍሬኒያ በዘር ሊተላለፍ ይችላል ማለት ነው። በሽታው ከሚታይባቸው ሰዎች መሃል አንድ ሶስተኛዎቹ በህይወታቸው አንድ ጊዜ ብቻ አጋጥሟቸው የሚያልፍ ሲሆን በቀሩት ላይ ግን በተደጋጋሚ የሚከሰት ነው። በመጀመሪያ የሚታይባቸውም ከ15 እስከ 25 አመት የእድሜ ክልል ሳሉ ነው።
በሽታው በሚጀምርባቸው ጊዜያት ከሰዎች መነጠልን፣የመንፈስ መጨነቅን እና ምክንያት የሌለው ከፍተኛ ፍራቻን ያመጣል። ከዚያም ከሳምንታት እስከ አመታት ባለ ጊዜ ዉስጥ ተባብሶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል። በዚህ ጊዜ የሚከተሉትን ምልክቶች ማሳየት ይጀምራል ።
የስኪዞፈሪንያ ምልክቶች?

????በጣም የተጋነኑ ስሜቶች እና አስተውሎቶች
በገሃዱ አለም የሌሉ ድምጾችን መስማት፣ የሌሉ ነገሮችን ማየት መቅመስ ወይም ማሽተት በአጠቃላይ በቁም መቃዥት ይታይባቸዋል። ተገቢ ያልሆኑ ጸጸት ውስጥ ተዘፍቀው ልናገኛቸውም እንችላለን።
????ከእውነት የራቁ አስተሳሰቦች እና የተሳሳቱ እምነቶች
እነኚህ ታማሚዎች ‘የተለየ ስጦታና ሃይል አለኝ’ ወይም ‘ከሌሎች የምበልጥ ነኝ’ ሊሉ ይችላሉ። አለበለዚያ ‘ሰዎች እያሳደዱኝ ነው’ ብለው ሊሸሹ እና ሊደበቁ ሲጥሩም ይታያሉ።
????ከተገቢው በታች የተቀዛቀዙ ስሜቶች እና ፍላጎቶች
ስራ ለመስራት እና የየዕለት ተግባራትን ለማከናወን ፍላጎት ማጣት ፣ በሁሉም ነገር መሰላቸት ይስተዋልባቸዋል። በተጨማሪም ስሜታቸውን የመግለጽ ችሎታቸው በጣም ስለሚቀንስ የደነዘዘ ፊት ይታይባቸዋል ።ስለዚህ እንደጤናማው ሰው በሃዘን እና በደስታ ጊዜ ተገቢውን ስሜት ማንጸባረቅ አይችሉም።
????የንግግር መዛባት
የተዘበራረቁ እና ተያያዥነት የሌላቸውን ሃሳቦች በአንድ ጊዜ ስለሚናገሩ ከሰው ጋር መግባባት ይቸግራቸዋል።
ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች እና ጥንቃቄዎች?

በመግቢያው እንደተጠቀሰው ለአእምሮ ጤና የሚሰጠው ትኩረት ያነሰ በመሆኑ እና በብዛትም መንፈሳዊ ተደርጎ ሰለሚታይ ምልክቶች የከፋ ደረጃ ሳይደርሱ መቆጣጠር የሚቻልበት እድል ሲጠብ ይስተዋላል። ስለዚህ ግለሰቦች የራሳቸውንም ሆነ የወዳጅ ዘመዶቻቸውን የአእምሮ ጤና በመከታተል ያልተለመዱ የጸባይ ለውጦችንም በማስተዋል የህክምና ክትትል ማድረግ አለባቸው። ይህ በሽታው ሳይባባስ ለመቆጣጠር ስለሚረዳ እጅግ አስፈላጊ ነው። በተለይም በቤተሰብ ውስጥ ስኪዞፈሪንያ ያለበት ሰው ካለ የተቀሩት የቤተሰብ አባላት ለአእምሮ ጤናቸው ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል። ስኪዞፍሬኒያ ያለበት ሰው በሽታውን ስለሚያባብሱ ከአልኮል እና ከአደንዛዥ እጾች መቆጠብ ይኖርበታል።
በሽታውን ሙሉ ለሙሉ የሚያስወግድ ፈዋሽ መድሃኒት ባይኖርም ምልክቶቹን በቁጥጥር ስር በማድረግ በኑሮ ላይ የሚያመጣውን ተጽእኖ መቀነስ ስለሚቻል የስኪዞፈሪንያ ታማሚዎችን ወደ ህክምና ማምጣት እጅግ ጠቃሚ ነው።
በተጨማሪም የዚህንም ሆነ የሌሎች የአእምሮ ህመም ተጠቂ የሆኑ ሰዎችን ባልተገባ መልኩ እንደ ‘እብድ’ የመሰሉ ስያሜዎችን ሰጥቶ ማሸማቀቅ ግፋ ሲልም አካላዊ እና ጾታዊ ጥቃቶችን ማድረስ ማህበረሰባችን ሊያስወግደው የሚገባ እጅግ መጥፎ ልማድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። የአእምሮ ህሙማን እንደልብ፣ ኩላሊት እና ሳንባ ህሙማን ሁሉ የታመሙ ናቸውና እንክብካቤ እና ተገቢየህክምና ክትትል ሊደርግላቸው እንጂ ጥቃት ሊደርስባቸው አይገባም።












