ከመጠን በላይ መወፈር ከልክ በላይ የሆነ የሰውነት ስብ በማከማቸት የሚታወቅ የጤና እክል ሲሆን በጤና ላይ አሉታዊ ተጽእኖም ሲኖረው ህመም እና ሞት ሊያስከትል ይችላል።
የአለም ጤና ድርጅት መረጃዎች እንደሚያሳየው ከሆነ እ.ኤ.አ. በ 2016ዓ.ም. በአለም ላይ ዕድሜያቸው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ በሆናቸው አዋቂዎች ፣ 1.9 ቢሊዮን ያክሉ ከመጠን በላይ ክብደት ያላቸው ነበሩ። ከእነዚህ ውስጥ ከ650 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ውፍረት ያላቸው ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ1975 እና 2016 መካከል ያለው የአለም ውፍረት ስርጭት በሦስት እጥፍ ጭማሪ አሳይቷል። ከ1980 ጀምሮ ከመጠን በላይ ውፍረት ከ 70 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ በእጥፍ ጨምሯል። በአጠቃላይ 13% የሚሆነው የአለም አዋቂ ህዝብ (11% ወንዶች እና 15% ሴቶች) በ 2016 ከመጠን በላይ ወፍራም ነበሩ::

ወደ ኢትዮዽያ ሁኔታ ስንመጣ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ጎልማሶች የማእከላዊ ውፍረት ስርጭትን እና መንስኤዎችን በጋራ ለመወሰን የተደረገ ስልታዊ ግምገማ እና ሜታ-ትንተና እንደሚያሳየው አጠቃላይ የማዕከላዊ ውፍረት ስርጭት 37.31% ሲሆን ይህም ከፍ ያለ አኃዝ ነው።
BMI ምንድን ነው?

BMI የሰውነት ብዛት መረጃ ጠቋሚ ማለት ነው። የአንድ ግለሰብ ክብደት እና ቁመት ላይ በመመርኮዝ የሰውነት ስብን የሚያሰላ መለኪያ ነው። የአንድን ሰው ክብደት በኪሎግራም እና ቁመታቸውን ደሞ በሜትር ስኩዌር በማድረግ ከዛም በማካፈል (ኪግ/ሜ 2)ይሰላል። BMI በተለምዶ አንድ ሰው ከክብደት በታች፣ መደበኛ ክብደት፣ ከመጠን ያለፈ ክብደት ወይም ውፍረት መሆኑን ለማወቅ እንደ መመርመሪያ መሳሪያ ነው። BMI ለመለካት ቀላል፣ አስተማማኝ እና ከሰውነት ስብ እና የሰውነት ስብ ስብስብ መቶኛ ጋር የተቆራኘ ነው። BMI የአጠቃላይ የሰውነት ስብን ለመገመት ከሰውነት ክብደት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ግምት ይሰጣል።
ታዲያ ውፍረትን ለመመርመር የሚያስችሉ መስፈርቶች የትኞቹ ናቸው?
የሰውነት ብዛት መረጃ ጠቋሚ (BMI) ምደባዎች የልብና የደም ሥር በሽታ(CVD) ስጋት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በአሜሪካው ብሔራዊ የጤና ኢንስቲትዩት (NIH) እና የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ለነጭ፣ ስፓኒክ እና ጥቁር ግለሰቦች ተቀባይነት ያገኙ ለBMI የሚመከሩ ምደባዎች እኚህ ናቸው፡-
● ከክብደት በታች – <18.5 ኪ.ግ / ሜ 2
● መደበኛ ክብደት – ከ18.5 እስከ 24.9 ኪ.ግ / ሜ2
●ከመጠን በላይ ክብደት – ከ25.0 እስከ 29.9 ኪ.ግ/ሜ2
● ውፍረት – ≥30 ኪ.ግ / ሜ2
• ክፍል I – ከ 30.0 እስከ 34.9 ኪ.ግ / ሜ2
• ክፍል II – ከ 35.0 እስከ 39.9 ኪ.ግ / ሜ2
• ክፍል III – ≥40 ኪግ/ሜ2
ለውፍረት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው?

ዘር፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ለአዋቂዎች የዘር አስተዋፅኦ ከ40 እስከ 70 በመቶ ነው። አንድ ወጣት አንድ ወላጁ/ጇ ከመጠን በላይ ውፍረት ካለው፣ ከመጠን በላይ የመወፈር እድሉ/ሏ ከሌላቸው ጋር ሲነጻጸር ከሶስት እስከ አራት እጥፍ ይጨምራል። ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ሁለት ወላጆች መኖር ደሞ ከ10 እጥፍ በላይ ከመጠን በላይ የመወፈር አደጋ ጋር የተያያዘ ነው።
የማህበራዊ ሁኔታ፡ በሚገርም ሁኔታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ውፍረት ከፍተኛ ገቢ ባላቸው እና ከፍተኛ ትምህርት ባላቸው ሰዎች መካከል ዝቅተኛ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ደሞ ጤናማ ያኗኗር ሁኔታን እንደ አመጋገብ ስርአት ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድርግ(ለምሳሌ የእግረኛ መንገድ እና የመጫወቻ ሜዳ መገኘትን) ከመሳሰሉ የጤና ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።
እድሜ፡ አዋቂዎች ከ20 እስከ 65 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ቀስ በቀስ ክብደት ይጨምራሉ። ከዚያ በኋላ በአብዛኛዎቹ ሰዎች ክብደት ይቀንሳል፣ ይህ የክብደት መቀነስ ግን በከፊል የጡንቻን ብዛት በማጣት ነው።
የአኗኗር ዘይቤ፡ የአኗኗር ዘይቤዎች፣ እንደ አመጋገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (እና እንቅስቃሴ-አልባነት)፣ የእንቅልፍ ሁኔታ እና ሲጋራ ማጨስ ማቆም፣ ሁሉም ከክብደት መጨመር ጋር የተያያዙ ናቸው።
መድሐኒቶች፡ አንዳንድ የሳይኮሲስ መድኃኒቶች፣ ፀረ-ጭንቀቶች፣ ለመጣል ብሽታ የሚሰጡ መድኃኒቶች፣ ፀረ-ስኳር መድኃኒቶች እና የሆርሞን የወሊድ መከላከያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የተለመዱ መድኃኒቶች ከክብደት መጨመር ጋር ይያያዛሉ።
አንዳንድ የጤና እክሎች፡ የተወሰኑ የህክምና ሁኔታዎች እንደ ሃይፖታይሮዲዝም፣ ኩሺንግ ሲንድረም፣ ሃይፖታላሚክ ድክመቶች (ማለትም፣ ሃይፖታላሚክ ከመጠን ያለፈ ውፍረት የምንለው) እና የእድገት ሆርሞን እጥረትን ጨምሮ ከክብደት መጨመር ጋር ሊገናኙ ይችላሉ።
ከውፍረት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና አደጋዎች ምን ምን ናቸው?

1. የስኳር በሽታ
2. በደም ውስጥ ያለ የስብ መጠን መዛባት
3. ደም ግፊት
4. የልብ በሽታ
5. ስትሮክ
6. የደም መላሽ የደም ስር ውስጥ ደም መርጋት እና መሰንቀር
7. ካንሰር
8. የአጥንት እና መገጣጠሚያ ብግነት(Osteoarthritis)
9. ሪህ(Gout)
10. የሃሞት ከረጢት በሽታ እና ከአልኮል ጋር ያልተያያዘ የሰባ ጉበት በሽታ(nonalcoholic fatty liver disease)
11. የቃር በሽታ (GERD)
12. የስነ ተዋልዶ ችግሮች
13. የኩላሊት በሽታ
14. የኩላሊት ጠጠር
15. ሽንትን መቆጣጠር ያለመቻል በሽታ
16. ድባቴ
17. በእንቅልፍ ወቅት የትንፋሽ መቋረጥ(Obstructive sleep apnea)
18. አስም
19. ከቀዶ ጥገና በኋላ፣ በሆስፒታል ቆይታ፣ የመተንፈሻ አካላት፣ የቆዳ እና የጡንቻ ኢንፌክሽኖች
20. ሞት












