አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 12/2015፣ NBC ETHIOPIA -ነባሩ የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልም ስያሜውን ወደ “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል” በመቀየር እንደገና እንደሚመሠረት ተጠቁሟል፡፡

የደቡብ ብሄር፣ ብረሰቦችና ህዝቦች ክልል የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት፤ አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 12ኛውየኢትዮጵያ ክልል ሆኖ ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ ይመሠረታል፡፡
ነባሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ደግሞ ስያሜውን ወደ “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል” በመቀየር በዕለቱ እንደገና የሚመሠረት ይሆናል፡፡
የደቡብ ክልልን በሁለት ክልሎች የማደራጀቱ ሥራ በሶስት ምዕራፎች ሲከናወን ቆይቶ አሁን ወደማጠቃለያው መደረሱን የተናገሩት አቶ ጥላሁን፤ በዚህም ነባሩ የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የለውጥ ሥራዎች በማከናወን አዲሱን ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ደግሞ የማደራጀት ሥራዎች በመጠናቀቃቸውን ክልሎቹ ነሀሴ 13 በይፋ እንደሚመሠረቱ ተናግረዋል፡፡
ክልሎቹ ብዝሃ ማዕከላት እንዲኖራቸው በመወሰኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 6 ማዕከል ከተሞች የሚኖሩት ሲሆን ወላይታ ሶዶ፣ አርባምንጭ ፣ዲላ፣ ጂንካ፣ ሳውላ እና ከአራት ከተሞች ለማዕከልነት የተመረጡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ሆሳዕና፣ ቡታጅራ፣ ወልቂጤ፣ ወራቤ፣ ሀላባ ቆሊቶ፣ ዱራሜ እና ሳጃ ከተሞች ደግሞ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተመረጡ ሰባት የማዕከል ከተሞች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ሁሉም የተመረጡት ከተሞች እኩል የክልል ማዕከላት መሆናቸውን ጠቁመው፤ ወላይታ ሶዶ እና ሆሳዕና ከተሞች ደግሞ የክልሎቹ ርዕሰ መስተዳድሮች መቀመጫ እንደሚሆኑ አክለው ገልጸዋል፡፡
ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች ሲኖሩት ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ 5 ዞኖችና 1 ልዩ ወረዳ እንደሚኖሩት አመልክተው፤ ክልሎቹ ብዝሃ ቋንቋ የሚነገርባቸውና በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባቸው በመሆናቸው ክልሎቹ የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን ከስምምነት መደረሱን አመላክተዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ነባሩን ሕገ መንግሥት በማሻሻል እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዲስ ሕገ መንግስሥት ዛሬ ነሀሴ 12ቀን 2015ዓ.ም በሚካሄድ ጉባዔ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሕዝቦች መካከል የተፈጠረ አንድነትና ወንድማማችነት ከንብረት በላይ በመሆኑ ንብረት ክፍፍሉ እንዲሁም የሰው ሀብት የማጓጓዙ ሥራ በጋራ በወንድማማችነት መንፈስ እየተከናወነ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ኢ ፕ ድ ዘግቧል ::
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook -https://www.facebook.com/ethiopiannbc












