አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 4 /2015 | NBC ETHIOPIA-በኢኳዶር በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት ፈርናንዶ ቪላቪሴንሲዮ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በጥይት ተመትተው ተገደሉ።

የሃገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት አባሉ ፈርናንዶ ረቡዕ ዕለት በሰሜናዊቷ ኪቶ ቅስቀሳቸውን እንደጨረሱ ነው ጥቃቱ የተፈጸመባቸው።
እጩው ፕሬዚዳንት መኪና ውስጥ እየገቡ በነበረበት ወቅት አንድ ግለሰብ ወደፊት ተጠግቶ ጭንቅላታቸውን በጥይት እንደተመቱ ቢቢሲ ዘግቧል።
የ59 አመቱ ፖለቲከኛ በሶስት ጥይት ተመትተው መሞታቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
ጥቃት ፈጻሚው ከደህንነቶች ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በኋላም ህይወቱ ማለፉን ተገልፃል። በጥቃቱ ሌላ የምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ እና ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች ቆስለዋል ተብሏል።
በኢኳዶር ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እያንሰራራ የመጣው የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድኖች መበራከት የዘንድሮው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻም ዋነኛ ትኩረት ሆኗል።

ባለፈው ወር ከተደራጁ ወንጀሎች ጋር በተገናኘ በርካታ ግድያዎች መፈጸማቸውን ተከትሎም የሃገሪቱ መንግሥት በሶስት ግዛቶች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና የሰዓት እላፊ ገደብም ጥሏል።
የተገደሉት ፖለቲከኛ በምርጫ ዘመቻቸው በሃገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋውን ሙስና ለመቅረፍ መደረግ ያለበትን ጥረት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ባለትዳር እና የአምስት ልጆች አባት የሆኑት ፈርናንዶ በሃገሪቱ ውስጥ በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከስምንት እጩዎች መካከል አንዱ ነበሩ።
በሃና ተሰማ
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc












