
የአዲስ አበባ |የካቲት 11 2015 | NBC ETHIOPIA-ዛሬ የሚጀመረው 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በተለያዩ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የሕብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ይካሄዳል፡፡
“የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መቀላጠፍ” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው የዘንድሮ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 ወደ ሥራ የገባውንና 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ሕዝብ በንግድ ለማስተሳሰር የታለመውን የንግድ ቀጣና ይበልጥ ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ይመክራል።
በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በአፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ የተከሰተው ድርቅና ረሃብ እንዲሁም በዩክሬንና በሩስያ ጦርነት ምክንያት አደጋ ላይ የወደቀው የአህጉሪቱ የምግብ ዋስትና ችግር እልባት በሚሰጡ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ሌላው በትኩረት የሚያዩት አጀንዳ ነው፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የግብርና ሥራ ለማሳለጥና በአህጉሪቱ ዘመናዊ የእርሻ ሥራ በሚስፋፋባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተጠቁሟል። ይህም በዘላቂነት የአህጉሪቱን የምግብ ፍላጎት በራስ አቅም ለመሸፈን የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ይሆናል ተብሏል።
ባለፉት አሥር ዓመታት በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት የተጣለውን የረዥም ጊዜ ዕቅድ ከግምት በማስገባት የተሰሩ ሥራዎች ይገመግማል ተብሏል።
ለቀጣይ አሥር ዓመታት(2063) በተለያዩ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሊደረግባቸው በሚችሉ አንኳር ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጎ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ነው የተገለጸው።
በተለይም ደግሞ ዋና ዋና የሚባሉ ስኬቶችን በመገምገምና ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት መጪውን አሥር ዓመት የተሻለ ለመፈጸም የሚያስችል የትግበራ ማዕቀፍ እንደሚዘጋጅ ይጠበቃል።
በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ ኅብረቱ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ምክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ በቻድ፣ በካሜሮን፣ ኒጀር፣ በናይጄሪያ አካባቢው ከጽንፈኝነት ጋር በተያያዘ በርካታ የጸጥታ ችግሮች እየተከሰቱ ሲሆን ይህም ለበርካቶች ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።
በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ ክፍልም የትጥቅ ትግል መቀስቀሱ የተዘገበ ሲሆን ይህም አገሪቱን ከሚያዋስኑ አገራት ጋርም አለመረጋጋት ፈጥሯል። በሰሜን ሞዛምቢክ ያለው የጸጥታ ችግርም አሁንም እልባት ያላገኘ ጉዳይ ነው።
በመሆኑም የአፍሪካ ኅብረት በእነዚህና በሌሎች የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ምክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት









