ልክ በዛሬዋ ቀን ሰኔ 30 1939 ዓ.ም ታላቁ ባለቅኔ ፣ ጸሐፌ-ተውኔት ፣ አርበኛ ፣ የመዝሙርና የታሪክ ጸሐፊ የነበሩት የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ በተወለዱ 52 ዓመታቸው ህይወታቸው ያለፈበት ዕለት ነበር።
ዮፍታሔ የተወለደው ጐጃም ውስጥ ደብረኤልያስ አመደ ጉባ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ በ1887 ዓ.ም ነበር፡፡ ትምህርቱንም በቤተክርስቲያን ውስጥ የተማረ ሲሆን ፊደልን፣ ንባብን፣ መዝሙረ ዳዊትን፣ ዜማን፣ ጾመ ድጓ፣ ድጓ፣ ቅኔን ተምሮል፡፡
ትምህርቱን ሲጨርስም መምህር ሆኖ ተመረቀ። በሙያውም ለአምስት ዓመታት ካገለገለ በኋላ የሽማግሌዎችን ሹመት በመቀበል “ቀኝ ጌታ” ተባለ። በ 1908 ዓ.ም ወደ ራስ ኃይሉ (የጐጃም ገዢ) ዘንድ ማለትም ደብረማርቆስ ሄዶ ስራ ለመቀጠር ችሎታውን አሳየ። በችሎታውና ባለው የቀለም እውቀት ተደንቆ ተቀጠረ።
ግንቦት ወር 1910 ዓ.ም ዮፍታሔ ንጉሴ አዲስ አበባ መጣ። በቤተ-ክህነት ትምህርት እጅግ በሳል የተባለ አዋቂ በመሆኑ ስራ ለመያዝ ምንም አልተቸገረም። በ 1918 ዓ.ም ዮፍታሔ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በአማርኛ መምህርነት ተቀጠረ። እዚህ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ማስተማር ከጀመረ በኋላ ግጥሞችን እና መዝሙሮችን እንዲሁም ቴአትሮችን መስራት ጀመረ።
በቴአትር ፀሐፊነትና አዘጋጅነትም የተዋጣለት ሆነ። አፋጀሽኝ የተሰኘችው ቴአትሩና ሌሎችም ስመ ገናና እያደረጉት መጡ። በኢትዮጵያ ውስጥ ቴአትር በማስፋፋትና በማሳደግ ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀሰው ዮፍታሔ፣ በ 1919 ዓ.ም ሐምሌ 14 ቀን ከብላታ በቀለ ጋር ሆኖ በፈረንጅ አንተማመን የሚል ሀሳብ ያለው ቴአትር ሰርቶል፡፡
ዮፍታሔ በ 1925 ዓ.ም የቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆኖ ተሾመ። ዮፍታሔ ንጉሴ ስለ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያንም አርበኝነትና ተጋድሎ በመፃፍ የሚታወቅ ባለቅኔ ነበር። ዮፍታሔ አደገኛ ሰላይ ሆኖ ለሀገሩ ኢትዮጵያ አገልግሏል። ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ራሱን በልዩ ልዩ መልክ እየቀየረ በመምጣት ከአርበኞች ጋር ተገናኝቶ እና የሚፈልገውን መልዕክት አድርሶና ተቀብሎ ወደ ሱዳን ይመለስ ነበር። ለጃንሆይም መልዕክት ያስተላልፍ ነበር።
ከዚህ በኋላ ሥነ-ጥበብ ሚኒስቴር ውስጥ ስራ ተሰጠው፤ በወር ከ 150 ብር ደመወዝ ጋር። ግን አልሰራም አለ። ሐምሌ 16 ቀን 1934 ዓ.ም “እያዩ ማዘን” የተባለ ቴአትር ፃፈ። ቴአትሩ ደግሞ ከፍተኛ ብስጭቱን የገለፀበት ነበር።
ይህን ቴአትር የተገነዘቡት አፄ ኃይለስላሴ ውሣኔ የሰጡ ሲሆን ወዲያው ጥቅምት 18 ቀን 1935 ዓ.ም ዮፍታሔ ንጉሴ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አድርገው ሾሙት። ከዚህ በኋላም “ዕርበተ ፀሐይ” የተሰኘውን ቴአትሩን ፅፏል። ቴአትሩ የልዕልት ፀሐይ ኃይለስላሴን ሞት ምክንያት በማድረግ የተፃፈ ነበር። ዮፍታሔ ንጉሴ ሦስት ትዳሮችን በየጊዜው መስርቶ ነበር። ወ/ሮ ጥሩነሽ ደባን፣ ወ/ሮ ሙሉወርቅ ጠናን እና የመጀመሪያዋ የሴት ጋዜጠኛ የነበሩትን ደራሲ ሮማንወርቅ ካሳሁንን አግብቶ ነበር።
ዮፍታሔ በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ዓለም ውስጥ አጭር የሆነ ጊዜ ቢቆይም አብርቶ ያለፈው ብርሃን እጅግ ደማቅ ነበር። ይህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም ድንገት አሞት ሐኪም ቤት ሄዶ መርፌ ተወግቶ ተመልሷል። ህመሙ ከባድ ስላልነበር ከስራው አልቀረም። ማታም ከጓደኛው ከአቶ መሐሪ ካሣ ቤት ደህና ሲጫወት አምሽቶ ወደ ቤቱ ገብቶ ተኝቷል። ሆኖም ጧት ሰራተኛው ቁርስ ሰርታ ብትጠብቀው አልመጣም። ታላቁ የኪነ-ጥበብ ሰው ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም በ 52 ዓመቱ እስከወዲያኛው አሸልቦል።
በ-ሔርሜላ ተመስገን












