ልክ በዚች ቀን ሰኔ 25 ቀን 1925 ዓ∙ም ደራሲና ጋዜጠኛ አቤ ጉበኛ ተወለዱ። በምዕራብ ጎጃም ዞን በአቸፈር ወረዳ በልዩ ስሙ ኮረንች አቦ በተባለ ቀበሌ ከአባታ አቶ ጉበኛ አምባየነ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ይጋርዱ በላይ የተገኙ ናቸው ደራሲና ጋዜጠኛ።
ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በመጀመሪያ የአብነት ትምህርት በይስማላ ደብረ ገነት ቅ/ጊ ቤ/ክርስቲያን ዜማ፣ ዳዊት እና ቅኔ ለ12 ዓመታት ተከታትለዋል። አቤ በዘመናዊ ትምህርቱን በዳንግላ ከተማ ይከታተል የነበረ ሲሆን፣ በ1946 ዓ.ም ዳንግላን ለቆ ወደ አ/አ በመሄድ ባዕታ ቤተክርስቲያን ተጠግቶ እንደ ቆሎ ተማሪ ሆኖ ቆይቶል።
አቤ ከልጅነቱ ጀምሮ ውስጡ የፁሑፍ ፍላጎት እና ችሎታ ስለነበረው በ1949 ዓ.ም “ከመቅሰፍት ሰራዊት ይጠንቀቅ ሰውነት” በሚል ርዕስ አነስተኛ የግጥም መፅሐፍ አሳትሟል። አቤ በ26 ዓመቱ በማስታወቂያ ሚኒስቴር በጋዜጠኝነት ተቀጥሮ ሰርቷል። በ1953 ዓ.ም ባሳተመው “የሮም አወዳደቅ” የተውኔት መፅሐፍ በወቅቱ ገበሬው በንጉሡ ስርአት ያለውን ብሶት እና ቁጭት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ፅሁፍ ነበር።
አቤ የሚፅፋቸው መፅሐፍ ለመንግሥት አስቸጋሪ በመሆናቸው በ 1955 ዓ.ም “አልወለድም” በፃፈበት ወቅት በመንግስት ከፍተኛ ክትትል ይደረግበት ነበር። በዚሁ ዓመት ባወጣው “የአመፅ ኑዛዜ” የተሰኘው ልብወለድ መፅሀፉ ተምረው ሆነ ሰርተው ሀብት ያገኙ ሰዎች ድሀ ወገኖቻቸውን እንዲረዱ የሚያሳስብ ነበር።
በሐምሌ 1956 “ሰይፈ ነበልባል” መፅሐፍ አሳትሟል። ይህ መፅሐፍ ልክ እንደ “አልወለድም” መፅሐፍ ይታገዳል በሚል ጥርጣሬ ህዝቡ መፅሐፍን ለመግዛት ከፍተኛ ርብርብ ያደረግ ነበረ። በ 2 ወር ውሰጥ ብቻ 4 ጊዜ በተደጋጋሚ ለህትመት በቋጥል። ይህ መፅሐፍ እስከ ደርግ ዘመን መንግስት ድረስ (1968 ዓ.ም) የተሸጠ ሲሆን፣ የደርግ መንግስት አገዛዝ ከመጣቱ በፊት አስቀድሞ የተጻፈና ትችትን ያስቀመጠ መፅሐፍም ነበር።
አቤ ፖለቲካዊ ማህበራዊ ሀይማኖታዊ ጉዳዮችን ለህዝቡ በፅሁፍ ያካሂደው የነበረው የብዕር ትግል በቂ አለመሆኑን በማሰብ፣ በ 1957 ዓ.ም ላይ በተካሄደው የህዝብ እንደራሴነት ምርጫ ለመወዳደር የ50 ሰዎች የድጋፍ ፊርማ አግኝቶ ነበር። ከ 1961 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ዓመታት በእስራት በነበረበት ወቅትም በእስር ቤት ያሳለፋቸውን ሁኔታዎች በመጽሃፍ መልክ አስፍሯል።
አቤ ጉበኛ በ 47 ዓመቱ የካቲት 2 ቀን 1972 ዓ.ም ህይወቱ አልፏል፡፡ የሶስት ልጅ አባት የሆነ ደራሲና ጋዜጠኛ አቤ ከሃያ በላይ መፅሐፍትን ለአንባቢዎች አድርሷል።
ሔርሜላ ተመስገን












