፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ነሐሴ 21 2016| NBC ETHIOPIA-በአለም ተፅእኖ መፍጠር ከቻሉ የቴክኖጂ ኩባንያ መስራቾች መካከል የቴሌግራሙ መስራች እና ባለቤት ፓቬል ቫለሪቪች ዱሮቭ አንዱ ነው፡፡
በተደጋጋሚ ከሚነሳበት የደህንነት እና በመረጃ ጥሰት ጉዳይ ጋር ተያይዞ የቴሌግራም አሰራር የወንጀል ስራዎች እንዳይደረስባቸው እና መከላከል እንዳይቻል የሚያደርግ ነው በሚል ባለቤቱ ቅዳሜ በፈረንሳይ በቁጥጥር ስር ውላል፡፡
የሩሲያው ማርክ ዙከርበርግ ተብሎ የሚጠራው የ39 አመቱ ትውልደ ሩሲያዊ ቢሊየነር ፓቬል ዱሮቭ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ቦርጌት አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር መዋሉን አለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

ፓቬል ቫለሪቪች ዱሮቭ ትውልዱ በሶቭየት ህብረት በሌኒንግራድ ኤስ ኤፍ ኤስ አር ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱንም በሴንት ፒተርስበርግ ስቴት ዩኒቨርሲቲ መከታተሉን የህይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡
ዱሮቭ በ 2023 በፎርብስ የቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ መካተት የቻለ ሲሆን በወቅቱ የሀብቱ መጠን 11.5 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ሀብቱ በአብዛኛው የተመራው በቴሌግራም ባለቤትነት ሲሆን በአሁኑ ሰአት የሀብት መጠኑ 15.5 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የፎርብስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ዱሮቭ እስከ 2013 ባሉት ጊዜያት ውስጥ በተለያዩ ሶፍትዌሮች ግንባታን ጀምሮ እስከ ስራ አስፈፃሚሚነት አገልግላል፡፡ በፈረንጆቹ 2013 ከታላቅ ወንድሙ ኒኮላይ ጋር በመሆን በመላው አለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚ ያለውን ቴሌግራም መስርቷል፡፡ ወንድማማቾቹ ቀደም ሲል ቪኬ የተሰኘው የሩስያ ማህበራዊ ድረ ገጽ መስርተው የነበር ቢሆንም በመንግስት ተወስዶባቸዋል፡፡ፓቬል የሩሲያ መንግስት የተቃዋሚ ገጾችን እንዲያጠፋ ጥያቄ የቀረበለት ሲሆን ጥያቄውን እደማይቀበለው ከገለጸ በኃላ የቀረውን ድርሻ በመሸጥ የመንግስትን ጫና በመቃወም ሩሲያን በ2014 ለቆ ወጥቷል፡፡ ቴሌግራም በብሪቲሽ ቨርጂን ደሴቶች እና በዱባይ እንደ limited liability (ኤል ኤል ሲ) ኩባንያ ተመዝግቦ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የ39 አመቱ ትውልደ ሩሲያዊ የፈጠራ ውጤት የሆነው ቴሌግራም እንደፌስ ቡክ፣ ዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ ከመሳሰሉት የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች ጋር መወዳደር የቻለ ሲሆን ጠንካራ የመረጃ ጥበቃ ያለው በመሆኑ በተለያዩ ሃያላን ሀገራት መሪዎች ዘንድ ተመራጭ መሆን ችሏል፡፡

ይህ መተግበሪያ እስከ ሐምሌ 2024 ድረስ በየወሩ ከ950 ሚሊዮን በላይ ንቁ ተጠቃሚዎች እንደነበሩት የኩባንያው መረጃ ያመላክታል፡፡ መተግበሪያው ለአጠቃቀም ቀላል እና ፈጣን መሆኑን ተከትሎ በቡዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ነው፡፡ በተለይ በሩሲያ፣ በዩክሬን እና በቀድሞ የሶቬት ሀገራት ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ችላል፡፡ በሞስኮ እና በኪየቭ ባለስልጣናት በብዛት ጥቅም ላይ የዋለው በዩክሬን ውስጥ ስላለው የሩስያ ጦርነት ወሳኝ የመረጃ ምንጭ ሆኗል::
አንዳንድ ተንታኞች መተግበሪያውን ለጦርነቱ “ምናባዊ የጦር ሜዳ” ብለው ሲጠሩት ይደመጣል፡፡ መተግበሪያውን ከተፅዕኖ መጠበቅ እና ተጠቃሚዎችን ከመንግሥት የመረጃ ጥያቄዎች መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን በተደጋጋሚ ዱሮቭ ሲገልፅም ይደመጣል፡፡
በአለም ላይ በርካታ የማህበራዊ ሚድያ ገፆች እና መተግበሪያዎች ሲገኙ አብዛኛዎቹ በተለይ ታዋቂና ተፅእኖ ፈጣሪ የሚባሉት የማህበራዊ ገፆች ባለቤትነታቸው በNATO አባል ሀገራት ከእነሱም ደግሞ በሃያሏ አሜሪካ ስር ይገኛሉ፡፡ ሀያላን ሀገራት እነዚህም በርካታ ተጠቃሚ ያላቸውን ድህረገፆችና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ ሲሞክሩም ይስተዋላል፡፡
ሀገራት መረጃን ለመንግስት በማጋራት ዙርያ ባላቸው ፖሊሲ ምክንያትም Telegram የተለያየ ቦታዎችን እንደ ዋና መስርያቤት HeadQuarter ሲጠቀም ይስተዋላል፡፡ ተቋሙ በ2014 መቀመጫውን በጀርመን በርሊን አድርጎ የነበር ሲሆን ተጽዕኖው ሲበረታበት ደግሞ በ2017 ወደ ዱባይ አዘዋውራል፡፡ ዱሮቭ በ2014 የትውልድ ሀገሩን ሩሲያን ለቆ ከወጣ በሃላ በተለያዩ ሀገራት በመዘዋወር ከአራት በላይ ዜግነትን ማግኘት ችላል፡፡ የሩስያ ዜግነቱን ትቶም የፈረንሳይ ዜግነት በ2021 ተቀብሏል፤ በአረብ ኢምሬትስ እና በቅዱስ ኪትስ ከተባለችው የካሪቢያን ደሴትም ዜግነት ማግኘት ችላል፡፡

በርካታ ዜግነቶችን የያዘው ዱሮቭ በቴሌግራም አሰራር ላይ ፈረንሳይን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት በደህንነት እና በመረጃ ጥሰት ጉዳይ ጥብቅ ቁጥጥር ሲያደርጉበት ቆይተዋል፡፡ ባሳለፍነው ግንቦት 2024 የአውሮፓ ህብረት የቴክኖሎጂ ተቆጣጣሪዎች ቴሌግራም ለአውሮፓ የኦንላይ የይዘት ቁጥጥር ተገዥ እንዲሆን እየተነጋገሩ መሆኑን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ ዱሮቭ ከአሜሪካዊው ጋዜጠኛ ቱከር ካርልሰን ለቀረበለት ጥያቄ “ከማንም ትዕዛዝ ከመቀበል ነጻ መሆንን እመርጣለሁ” ሲል በወቅቱ ተናግራል፡፡
ዱሮቭ ቀደም ብሎም በፈረንሳይ ለምርመራ ሲፈለግ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ከአዘርባጃን በመነሳት በግል ጄቱ ቦርጌት አውሮፕላን ማረፊያ ካረፈ በኋላ በደህንነት ሰዎች መያዙ ከሰሞኑ ትላልቅ ሚዲያዎች የዘገቡ ሲሆን አብይ ዜና ሆኗል፡፡ የፈረንሳይ ባለስልጣናት የቴሌግራም መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ፓቬል ዱሮቭ የመልእክት መላላኪያ መተግበሪያው የገንዘብ ማጭበርበርን እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ጨምሮ ወንጀለኛነትን ያመቻቻል በሚል ክስ እንደተመሰረተበት የፈረንሳይ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
የፈረንሳይ መንግስት በእስሩ ዙሪያ ምንም አይነት በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም እስከ አራት ቀናት ድረስ በእስር ሊቆይ እንደሚችል ተገልጿል። የዋና ስራ አስፈፃሚው በቁጥጥር ስር መዋል በርካቶችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ የX ባለቤቱና ኢሎን ማስክ የቴሌግራም ዋና ስራ አስፈፃሚ መታሰር በአውሮፓ የመናገር ነጻነት ጥቃት እየተሰነዘረበት ነው ሲል ተችቷል፡፡
የመልዕክት መላላኪያ እና የማህበራዊ ሚዲያን አላግባብ በመጠቀም ባለቤቱን ተጠያቂ ማድረግ ዘበት መሆኑን ቴሌግራም ባወጣው መግለጫ ገልጿል። እንዲሁም ፓቬል ዱሮቭ ምንም የሚደብቀው ነገር የለም ፤ በተደጋጋሚ በአውሮፓ ውስጥ ይጓዛል ፤ ስለዚህ አፋጣኝ መፍትሄ እየጠበቅን ነው ሲል ቴሌግራም በመግለጫው ገልፃል፡፡
የአሜሪካ የደህንነት ቢሮ CIA በNATO በዋናነት በፈረንሳይ በኩል የቴሌግራምን እጅ በመጠምዘዝ የሰዎችን መረጃ አሳልፈው እንዲሰጡ ተደጋጋሚ ጫናዎችን እና መለማመጦችን ያደረገ ቢሆንም ሙከራዎቹ ሊሳካ እንዳልቻለ ነው ዘገባዎች የሚጠቁሙት፡፡












