፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 30 2016| NBC ETHIOPIA- አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጊዜው ይዟቸው ከመጡ አስደናቂ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል አንደኛው ነው፡፡
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አሊያም ሰው ሰራሽ አስተውሎት ባደጉት ሀገራት የተለያዩ ግልጋሎቶችን መስጠት ከጀመረ ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ ሲሆን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በስፋት አገልግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡
ቴክኖሎጂው ማንኛውንም ስራ በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን አይነተኛ ሚናን በመወጣት ላይ የሚገኝ ሲሆን በሀገራት ኢኮኖሚ እድገት ላይ የሚኖረው ድርሻም ከፍተኛ ነው፡፡
ምንም እንኳን ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለሀገራት ኢኮኖሚም ሆነ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ቢታመንበትም በአንጻሩ ደግሞ የስራ አጥ ዜጎችን ቁጥር በእጅጉ እንዲጨምር ያደርጋል የሚሉ አስተያየቶችም በተደጋጋሚ ይደመጣል፡፡
ባለንበት የፈረንጆቹ አመት 2024 ከግንቦት ወር ጀምሮ በዚሁ የቴክኖሎጂ ውጤት ምክንያት ከ4 ሺህ 600 የሚልቁ ሰዎች ከስራ ገበታቸው ውጭ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
ቴክኖሎጂው በአርት ኢንደስትሪውም ላይ ቢሆን ያመጣቸው በርካታ ፋኢዳዎች እንዳሉ ሁሉ በዘርፉ የሚገኙ ባለሙያዎች እንጀራ ላይ አደጋንም የደቀነ ሆኗል፡፡

በተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች የዘርፉ ባለሙያዎች ውስጥ 36 በመቶ የሚሆኑት የትርጉም ባለሙያዎች ስራቸውን በዚሁ ቴክኖሎጂ ምክንያት ሲያጡ 40 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ገቢያቸው እንዲቀንስ አድርጓል ተብሏል፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸው በቪዲዮ ጌም ስራ የተሰማሩ አዘጋጆች ቴክኖሎጂው ባስከተለው ጣጣ ገፈት ቀማሽ መሆናቸው ነው የተነገረው፡፡ባለሙያዎቹ በሚሰሩ ፊልሞች ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ንድፎችን የሚያወጡ ሲሆን በመቀጠልም ከነዚህ ንድፎች 2ዲ ወይም 3ዲ ሞዴሎችን ይፈጥራሉ፡፡
ይህም በሚሰራው ፊልም ላይ የተመልካቾችን ስሜት በሚገባ ለመቆጣጠር ያስችላሉ፡፡የዚህ ዘርፍ አዘጋጆች ናቸው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በስራችን ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው በሚል ስጋት ወደ ስራ ማቆም አድማ የገቡት፡፡የሆሊውድ የቪዲዮ ጌም አዘጋጆች የስራ ማቆም አድማ ላይ የሚገኙ ሲሆን አድማውን ለማድረግ የወሰኑት በቀረበላቸው አዲስ ውል ውስጥ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጥበቃ ላይ ስጋት እንዳላቸው በመጥቀስ ነው።

እንደ ዋርነር ብሮስና ዋልት ዲስኒ ያሉ ዋነኞቹ የቪዲዮ ጌም ሰሪዎች በሆሊውድ አርቲስቶች በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አጠቃቀም ላይ አድማ የገጠማቸው ተቋማት ናቸው፡፡በኩባንያዎቹ ከ2ሺህ 500 በላይ የቪዲዮ ጌም አዘጋጆችን ከሚወክሉ የተዋንያንና የጸሐፊዎች ማህበራት ጋር አዲስ ውልን አስመልክቶ አንድ ዓመት ተኩል ገደማ ችግሩን አስመልክቶ ንግግር ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች እንደ ደሞዝና የስራ ደህንነት ባሉ በርካታ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ቢገልጹም ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ባለው ጉዳይ ላይ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ባለመቻላቸው ለስምምነቱ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል።
ለድርድር ከቀረቡ 25 ጉዳዮች መካከል በ24ቱ ላይ የጋራ መግባባት ላይ ቢደርሱም ኤ አይን በተመለከተ ያለው ሀሳብ ውይይቱ ሙሉ በሙሉ በስምምነት እንዳይቋጭ እንቅፋት ፈጥሯል ነው የተባለው፡፡
የባለሙያዎቹ ማህበራት ተወካዮች “ኩባንያዎቹ አባላቶቻችንን ለመጉዳት አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን አላግባብ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ውል አንፈቅድም” ሲሉ ተከራክረዋል፡፡












