፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 19 2016| NBC ETHIOPIA- የአውሮፓ ህብረት ትላልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችንለመቆጣጠር የወጣውን ህግ ግዙፉ የአፕል ኩባንያ ጥሷል ሲል ከሰሞኑ ክስ አቅርቧል።
የአፕል ኩባንያ የአፕ ስቶር ተጠቃሚዎች በአፕስቶር ማስፈንጠሪያዎች አማካኝነት ቅናሽ የሚያገኙባቸው አማራጮችን በመገደብ ነው ክስ የቀረበበት፡፡ ይህም የአውሮፓ ህብረት ያስቀመጠው የዲጂታል ገበያ ዘርፉን ፍትሃዊ ለማድረግ ያለመውን የDigital Markets Act ወይም ህግ የሚጻረር ነው ብሎታል፡፡
ኩባንያውም ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ከዓለም አቀፍ ዓመታዊ ገቢ እስከ 10% ቅጣት ሊጠብቀው እንደሚችል ከወዲው ተገልጿል ።
ይህንንም ጥፋት የሚደግም ከሆነ ህብረቱ የሚጥልበት ቅጣት ኩባንያው ከአለም አቀፍ ገበያው ከሚያገኘው ገቢው ወደ 20% ሊጨምር ይችላል ነው የተባለው።
የአውሮፓ ኮሚሽን አፕል ኩባንያ ከሚያስተዳድራቸው ውጪ የሆኑ ቅናሽ ያላቸውን መተግበሪያዎች ለደንበኞች ማሳወቅ መቻል አለበት ሲል አሳስቧል።የDigital Markets Act በፈረንጆቹ መጋቢት ወር ላይ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን የእርስ በርስ ውድድር ለመቆጣጠር ስራ ላይ የዋለ ህግ ነው።
የአውሮፓ ህብረት የውድድር እና የዲጂታል ኃላፊ የሆኑት ማርግሬቴ ቬስታገር በሰጡት መግለጫ የዲኤምኤ ህግ ለመተግበሪያ አበልጻጊዎች እንዲሁም ደግሞ ለሸማቾች የተሻሉ ቅናሾችን እንዲያውቁ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

ኮሚሽኑ በጊዜያዊነት አረጋገጥኩት እንዳለው በApple’s app store ህግ መሰረት ተጠቃሚዎች በአፕስቶር ማስፈንጠሪያዎች አማኝነት ቅናሽ የሚያገኝባቸው አማራጮችን እንዲጠቀሙ እድል የሰጡ አይደሉም።
ኮሚሽኑ የአፕል ኩባንያን በአዲሱ የዲጂታል ገበያ ህግ ጥሰት ሲከስ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በዚያ ወር ኮሚሽኑ በአፕል በጎግል አልፋቤት እና በፌስቡክ ሜታ የአውሮፓ ህብረትን ህግ ባለማክበር ተጠርጥሮ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
የአፕል አዲስ የኮንትራት መስፈርቶች ዲኤምኤ ህግ የጣሱ ናቸው ሲል ኮሚሽኑ በተጨማሪ በአፕል ኩባንያ ላይ ሌላ ምርመራ እንደከፈተ ገልጿል። አፕል በበኩሉ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ከዲኤምኤ ህግ ጋር ለመስማማት በርካታ ለውጦችን አድርጓል. ዕቅዳችን ሕጉን እንደሚያከብር እርግጠኛ ነን ሲል ኩባንያው አሳውቋል።
በ-ሀይማኖት ወርቁ












