፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 27 2016| NBC ETHIOPIA- አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰው ልጆች ህይወት ውስጥ ያለው ወሳኝ ሚና እየጨመረ መጥቷል። ተፅዕኖው በተለያዩ ዘርፎች ላይ በብዛት እየተስተዋለ ነው። ይህ ቴክኖሎጂ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ለሰው ልጅ የሚሰጥ ቢሆንም የጥቅሙን ያህሉም አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በቅርቡ ይፋ የተደረጉት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ውጤቶች የሆኑት ቻትጂፒቲ እና ባርድ በሰከንዶች ውስጥ የተለያዩ ምንጮች በመጠቀም አንድ ሰው የሚጠይቃቸውን መረጃዎች የሚያቀርቡ ናቸው። በዚህም በአንድ ሰው የተዘጋጁ የሚመስሉ የኮምፒውተር ኮዶች መቀመር፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ጽሑፎችን ማቅረብ እንዲሁም ግጥሞችን ሳይቀር መጻፍ የሚችሉ ናቸው።
በተጨማሪም ቻትጂፒቲ እና ባርድ የተባሉት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚያቀርቧቸው መረጃዎች ትክክለኛነታቸው አጠያያቂ ሊሆን ስለሚችል የአሳሳች መረጃ ስርጭትን ሊያስፋፉ ይችላሉ የሚል ስጋቶች ሲሰሙ ቆይተዋል፡፡ ድምጽ በማስመሰል ማጭበርበር ሊስፋፋ እና የቪዲዮ ምስሎችን በመፍጠር የሐሰት ዜና እንዲስፋፋ በር እየከፈተ መምጣጡን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ከሰሞኑም ወጣት መራጮች አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን አላግባብ በመጠቀም የውሸት እና የተሳሳተ መረጃዎችን በቲክ ቶክ እያስፋፋ መሆኑን ተገልፃል፡፡
ወጣት መራጮች በአለም ላይ በሚከናወኑ ቁልፍና ወሳኝ በሆኑ ምርጫዎች ላይ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በመጠቀም የፓርቲ መሪዎችን ምስል በመጠቀም የተሳሳቱ መረጃዎችን እና አላግባብ የሆኑ አስተያየቶችን የሚያሳዩ የውሸት ፈጠራ ቪዲዎችን በመስራት እያጋሩ መሆኑን ቢቢሲ ሰራሁት ባለው ጥናት አስታውቋል፡፡
ቲክ ቶክ በሀገራት በሚደረጉ ትላልቅ ምርጫዎች ላይ ሰዎች ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩበት አዲስ ማህበራዊ ሚዲያ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለወጣት መራጭ ተከታዮቻቸው ለመድረስ በመተግበሪያው ላይ ሜም መጀመራቸውን ነው የተገለፀው፡፡ በአሁኑ ሰአት ታዋቂ የአለማችን ፖለቲከኞች ማህበራዊ ሚድያውን በመጠቀም እና የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው እንዲታገድ የወሰኑበትን ቲክቶክ የተቀላቀሉ ሲሆን በስአታት ውስጥ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ተከታይ ማግኘት ችለዋል፡፡

ቲክ ቶክን የሚጠቀሙ ወጣቶች ከአስቂኝ ምስሎች ጎን ለጎን ለአሳሳች እና ከፋፋይ ይዘት እየተጋለጡ መሆኑን ቢቢሲ ይፋ ባደረገው መረጃ አስታውቋል፡፡ ከተማሪዎች እና ከፖለቲካ አራማጆች ጀምሮ እስከ ኮሜዲያን እና ማንነታቸው ያልታወቁ ቦት መሰል አካውንቶች በሁሉም ሰው እየተጋራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እይታዎችን ያገኘውን የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሪሺ ሱናክ በአርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ የተፈጠረ ቪዲዮ በማህበራዊው ሚድያው ላይ መሸራጨቱንና በመቶ ሺ እይታዎች ማግኘቱን ቢቢሲ አስታውሳል፡፡ ይህ ተንቀሻቃስ ምስል በምርጫ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት በማስመሰል የተሰራጨው የውሸት ምስል መሆኑን በዘገባው ተጠቁማል፡፡

ቲክ ቶክ ለቢቢሲ እንደተናገረው ለዩናይትድ ኪንግደም አጠቃላይ ምርጫ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በተጨማሪም የውጭ ምርጫን ጣልቃገብነት ለመቋቋም ተጨማሪ ፖሊሲዎችን እያረቀቀ እንደሆነ ቲክቶክ አስታውቋል፡፡ 97 በመቶ የሚሆኑትን ስለ ምርጫዎች እና የዜግነት ጉዳዮች የተመለከቱ እና የተሳሳተ መረጃ የያዙ ቪዲዮዎችን ማንም ሰው ከማየቱ በፊት መሰረዙን ኩባንያው ይፋ አድርጓል፡፡
ካለፈው የኢንግሊዝ ምርጫ በኋላ የቲክ ቶክ ተጠቃሚዎች በሀገሪቱ በተከታታይ አመት በፍጥነት ማደጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የሀሰት ምስሎችን እየፈጠሩ የሚያሰራጩት በርካታ ወጣቶች በአሥራዎቹ መጨረሻ ወይም በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ይገኛሉ የተባለ ሲሆን የፖለቲካ ቪዲዮዎችን በመፍጠር እያጋሩ ነው መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል።












